text
stringlengths
4
267
ሥሩ መሬት ውስጥ ቢያረጅ፣ጉቶውም አፈር ውስጥ ቢበሰብስ፣
የውኃ ሽታ ሲያገኝ ያቆጠቁጣል፤እንደ አዲስ ተክልም ቅርንጫፎች ያወጣል።
ሰው ግን ይሞታል፤ አቅም አጥቶም ይጋደማል፤ሰው ሲሞት የት ይገኛል?
ውኃ ከባሕር ውስጥ ይጠፋል፤ወንዝም ፈስሶ ይደርቃል።
ሰውም ያንቀላፋል፤ ደግሞም አይነሳም። ሰማይ እስከሚያልፍ ድረስ አይነቁም፤ከእንቅልፋቸውም አይነሱም።
ምነው በመቃብር ውስጥ በሰወርከኝ!ቁጣህ እስኪያልፍ ድረስ በሸሸግከኝ!ቀጠሮም ሰጥተህ ባስታወስከኝ!
ሰው ከሞተ በኋላ ዳግመኛ በሕይወት ሊኖር ይችላል? እፎይታ የማገኝበት ጊዜ እስኪደርስ ድረስ፣የግዳጅ አገልግሎት በምፈጽምበት ዘመን ሁሉ በትዕግሥት እጠብቃለሁ።
አንተ ትጣራለህ፤ እኔም እመልስልሃለሁ። የእጅህን ሥራ ትናፍቃለህ።
አሁን ግን እርምጃዬን ሁሉ ትቆጥራለህ፤ኃጢአቴን ብቻ ትመለከታለህ።
መተላለፌ በከረጢት ውስጥ ታሽጓል፤በደሌንም በሙጫ ታሽጋለህ።
ተራራ እንደሚወድቅና ተፈረካክሶ እንደሚጠፋ፣ቋጥኝም ከስፍራው እንደሚወገድ፣
ውኃ ድንጋይን እንደሚቦረቡር፣ጎርፍም የምድርን አፈር አጥቦ እንደሚወስድ፣አንተም ሟች የሆነውን ሰው ተስፋ አጥፍተሃል።
እስኪጠፋ ድረስ በእሱ ላይ ታይልበታለህ፤ገጽታውን ለውጠህ ታሰናብተዋለህ።
ልጆቹ ክብር ቢያገኙም እሱ ይህን አያውቅም፤ውርደት ሲደርስባቸውም ልብ አይልም።
ሕመም የሚሰማው በሥጋ ሳለ ብቻ ነው፤የሚያዝነው በሕይወት ሳለ ብቻ ነው።”
“ብር የሚወጣበት ቦታ፣ወርቅም የሚነጠርበት ስፍራ አለ፤
ብረት ከመሬት ውስጥ ይገኛል፤መዳብም ከዓለት ቀልጦ ይወጣል።
ሰው ጨለማን ያሸንፋል፤ማዕድን ለማግኘትበጨለማና በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እስከ ወሰኑ ድረስ ፍለጋ ያካሂዳል።
ሰዎች ከሚኖሩበት ክልል ርቆ በሚገኝ ስፍራ፣ሰዎች ከሚመላለሱበት አካባቢ ርቀው በሚገኙ የተረሱ ቦታዎች ጥልቅ ጉድጓድ ይቆፍራል፤አንዳንድ ሰዎች በገመድ ወደዚያ ይወርዳሉ፤ ተንጠልጥለውም ይሠራሉ።
በምድር ላይ እህል ይበቅላል፤ከታች ግን ምድር በእሳት የሆነ ያህል ትታመሳለች።
በዚያ በድንጋዮቹ ውስጥ ሰንፔር ይገኛል፤በአፈሩም ውስጥ ወርቅ አለ።
ወደዚያ የሚወስደውን መንገድ የትኛውም አዳኝ አሞራ አያውቀውም፤የጥቁር ጭልፊትም ዓይን አላየውም።
ግርማ የተላበሱ አራዊት አልረገጡትም፤ብርቱ አንበሳም በዚያ አላደባም።
ሰው የባልጩት ድንጋይ በእጁ ይመታል፤ተራሮችንም ከሥር መሠረታቸው ይገለብጣል።
በዓለት ውስጥ የውኃ ቦዮች ይሠራል፤ዓይኑም ውድ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ ያያል።
ወንዞች የሚፈልቁባቸውን ቦታዎች ይገድባል፤የተሰወረውንም ነገር ወደ ብርሃን ያወጣል።
ይሁንና ጥበብ የት ልትገኝ ትችላለች?ማስተዋል የሚገኘውስ ከየት ነው?
ማንም ሰው ዋጋዋን አይገነዘብም፤በሕያዋንም ምድር ልትገኝ አትችልም።
ጥልቁ ውኃ ‘እኔ ውስጥ የለችም!’ ይላል፤ ባሕሩም ‘በእኔ ዘንድ አይደለችም!’ ይላል።
እሷን በንጹሕ ወርቅ መግዛት አይቻልም፤በብርም ልትለወጥ አትችልም።
በኦፊር ወርቅም ሆነብርቅ በሆነው ኦኒክስና በሰንፔር ልትገዛ አትችልም።
ወርቅና መስተዋት ከእሷ ጋር ሊወዳደሩ አይችሉም፤ምርጥ ከሆነ ወርቅ በተሠራ ዕቃም እሷን መለወጥ አይቻልም።
ዛጎልና ክሪስታል ጨርሶ አይወዳደሯትም፤ጥበብ በከረጢት ሙሉ ካለ ዕንቁ ትበልጣለችና።
የኢትዮጵያ ቶጳዝዮን ከእሷ ጋር ሊወዳደር አይችልም፤በንጹሕ ወርቅ እንኳ እሷን መግዛት አይቻልም።
ታዲያ ጥበብ ከየት ትመጣለች?ማስተዋል የሚገኘውስ ከየት ነው?
ከሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ ዓይን ተሰውራለች፤በሰማያት ከሚበርሩ ወፎችም ተሸሽጋለች።
ጥፋትና ሞት፣‘ወሬዋን ብቻ በጆሯችን ሰምተናል’ ይላሉ።
ወደ እሷ የሚወስደውን መንገድ የሚረዳው አምላክ ነው፤መኖሪያዋን የሚያውቀው እሱ ብቻ ነው፤
እሱ እስከ ምድር ዳርቻ ይመለከታልና፤ከሰማያትም በታች ያለውን ሁሉ ያያል።
የነፋስን ኃይል በወሰነ ጊዜ፣ውኃዎችንም በለካ ጊዜ፣
ለዝናብ ሥርዓትን ባወጣ ጊዜ፣ነጎድጓድ ለቀላቀለ ጥቁር ደመና መንገድን ባዘጋጀ ጊዜ፣
ያኔ ጥበብን አያት፤ ደግሞም ገለጻት፤መሠረታት፤ እንዲሁም መረመራት።
ሰውንም እንዲህ አለው፦ ‘እነሆ፣ ይሖዋን መፍራት ጥበብ ነው፤ከክፉም መራቅ ማስተዋል ነው።’”
ቴማናዊው ኤሊፋዝ እንዲህ ሲል መለሰ፦
“ሰው አምላክን ሊጠቅመው ይችላል? ማስተዋል ያለውስ ሰው ምን ይፈይድለታል?
ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ አንተ ጻድቅ መሆንህ ግድ ይሰጠዋል?ወይስ በንጹሕ አቋም መመላለስህ እሱን ይጠቅመዋል?
አክብሮት ስላሳየህ ይቀጣሃል?ደግሞስ ፍርድ ቤት ያቀርብሃል?
ይህን የሚያደርገው የሠራኸው ክፋት ታላቅ ስለሆነ፣በደልህም ማብቂያ ስለሌለው አይደለም?
ያላንዳች ምክንያት ከወንድሞችህ ላይ መያዣ ትወስዳለህና፤ሰዎችንም ልብሳቸውን ገፈህ ራቁታቸውን ታስቀራለህ።
ለደከመው ሰው የሚጠጣ ውኃ አልሰጠህም፤የራበውንም ሰው ምግብ ነፍገሃል።
ምድሪቱ የኃያል ሰው ንብረት ነች፤የታደለም ሰው ይኖርባታል።
አንተ ግን መበለቶችን ባዶ እጃቸውን ሰደሃል፤አባት የሌላቸውንም ልጆች ክንድ ሰብረሃል።
ከዚህም የተነሳ በወጥመድ ተከበሃል፤ድንገተኛ ሽብርም ያስደነግጥሃል፤
በመሆኑም ማየት እንዳትችል ጨለማ ውጦሃል፤ጎርፍም አጥለቅልቆሃል።
አምላክ የሚኖረው ከፍ ባለው ሰማይ አይደለም? በሰማያት ያሉ ከዋክብትም ሁሉ ምን ያህል ከፍ ያሉ እንደሆኑ ተመልከት።
አንተ ግን እንዲህ ብለሃል፦ ‘አምላክ ምን ያውቃል? በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሊፈርድ ይችላል?
በሰማይ ክበብ ላይ ሲራመድ፣ማየት እንዳይችል ደመናት ይጋርዱታል።’
ክፉ ሰዎች የሄዱበትን፣የጥንቱን መንገድ ተከትለህ ትሄዳለህ?
እነሱ ጊዜያቸው ሳይደርስ ሞት ነጥቋቸዋል፤መሠረታቸው በጎርፍ ተጠራርጎ ሄዷል።
እውነተኛውን አምላክ ‘አትድረስብን!’ ደግሞም ‘ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በእኛ ላይ ምን ሊያደርግ ይችላል?’ ይላሉ።
ሆኖም ቤቶቻቸውን በመልካም ነገሮች የሞላው እሱ ነው። (እንዲህ ዓይነቱ ክፉ ሐሳብ ከእኔ የራቀ ነው።)
ጻድቅ ይህን አይቶ ይደሰታል፤ንጹሕ የሆነውም ሰው ይሳለቅባቸዋል፤ እንዲህም ይላቸዋል፦
‘ተቃዋሚዎቻችን ጠፍተዋል፤ከእነሱ የቀረውንም እሳት ይበላዋል።’
እሱን እወቅ፤ ከእሱም ጋር ሰላም ይኖርሃል፤እንዲህ ካደረግክ መልካም ነገሮች ታገኛለህ።
ሕጉን ከአፉ ተቀበል፤ቃሉንም በልብህ አኑር።
ሁሉን ቻይ ወደሆነው አምላክ ብትመለስ ትታደሳለህ፤ክፋትን ከድንኳንህ ብታርቅ፣
ወርቅህን አፈር ውስጥ፣የኦፊርንም ወርቅ ዓለታማ ሸለቆ ውስጥ ብትጥል፣
ያን ጊዜ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ወርቅናጥራት ያለው ብር ይሆንልሃል።
በዚህ ጊዜ ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ደስ ትሰኛለህና፤ፊትህንም ወደ አምላክ ቀና ታደርጋለህ።
ትለምነዋለህ፤ እሱም ይሰማሃል፤ስእለትህንም ትፈጽማለህ።
ለማድረግ ያሰብከው ነገር ሁሉ ይሳካልሃል፤በመንገድህም ላይ ብርሃን ይበራል።
በእብሪት ስትናገር ትዋረዳለህና፤ትሑት የሆነውን ግን ያድነዋል።
እሱ ንጹሕ የሆኑትን ያድናል፤ስለዚህ እጅህ ንጹሕ ከሆነ በእርግጥ ትድናለህ።”
ቴማናዊው ኤሊፋዝ እንዲህ ሲል መለሰ፦
“ጥበበኛ ሰው ከንቱ በሆነ ንግግር ይመልሳል?ወይስ በምሥራቅ ነፋስ ሆዱን ይሞላል?
በማይረባ ቃል መውቀስ ምንም ዋጋ የለውም፤ደግሞም ወሬ ብቻውን ምንም ጥቅም የለውም።
አንተ ፈሪሃ አምላክን ታጣጥላለህና፤ስለ አምላክ ማሰብም ዋጋ የለውም ትላለህ።
በደልህ በምትናገረው ነገር ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል፤ተንኮል ያዘለ ንግግር መናገርም ትመርጣለህ።
እኔ ሳልሆን የገዛ አፍህ ይፈርድብሃል፤የገዛ ከንፈሮችህ ይመሠክሩብሃል።
ለመሆኑ ከሰው ሁሉ በፊት የተወለድከው አንተ ነህ?ወይስ የተወለድከው ከኮረብቶች በፊት ነው?
የአምላክን ሚስጥር ትሰማለህ?ወይስ ጥበብ ያለህ አንተ ብቻ ነህ?
እኛ የማናውቀው አንተ ግን የምታውቀው ምን ነገር አለ? ደግሞስ እኛ የማናስተውለው አንተ ግን የምታስተውለው ምን ነገር አለ?
የሸበቱም ሆኑ በዕድሜ የገፉ፣እንዲሁም ከአባትህ በዕድሜ እጅግ የሚበልጡ ከእኛ ጋር አሉ።
የአምላክ ማጽናኛ፣ወይም በለሰለሰ አንደበት የተነገረህ ቃል አነሰህ?
ልብህ ለምን ይታበያል?ዓይኖችህስ ለምን በቁጣ ይጉረጠረጣሉ?
በአምላክ ላይ ተቆጥተሃልና፤እንዲህ ያሉ ቃላትም ከገዛ አፍህ ወጥተዋል።
ንጹሕ ይሆን ዘንድ ሟች የሆነ ሰው ምንድን ነው?ወይስ ጻድቅ ይሆን ዘንድ ከሴት የተወለደ ሰው ምንድን ነው?
እነሆ፣ በቅዱሳኑ ላይ እምነት የለውም፤ሰማያትም እንኳ በፊቱ ንጹሐን አይደሉም።
ታዲያ ክፋትን እንደ ውኃ የሚጠጣ፣አስጸያፊና ብልሹ የሆነ ሰውማ እንዴት ሊታመን ይችላል?
አዳምጠኝ! እኔ አሳውቅሃለሁ። ያየሁትን እናገራለሁ፤
ጥበበኛ ሰዎች ከአባቶቻቸው ሰምተው የተናገሩትን፣ደግሞም ከሌሎች ያልሸሸጉትን ነገር እነግርሃለሁ።
ምድሪቱ የተሰጠችው ለእነሱ ብቻ ነበር፤በመካከላቸውም ባዕድ ሰው አላለፈም።
ክፉ ሰው ዕድሜውን ሁሉ፣ለጨቋኙ በተመደቡት ዓመታት በሙሉ ይሠቃያል።
አስፈሪ ድምፆችን ይሰማል፤በሰላም ጊዜ ወራሪዎች ጥቃት ይሰነዝሩበታል።
ከጨለማ እንደሚያመልጥ አያምንም፤ሰይፍም ይጠብቀዋል።
‘ወዴት ነው?’ እያለ ምግብ ፍለጋ ይቅበዘበዛል፤ የጨለማ ቀን እንደደረሰ በሚገባ ያውቃል።
ጭንቀትና ሥቃይ ያሸብሩታል፤ጥቃት ለመሰንዘር እንደተዘጋጀ ንጉሥ ያይሉበታል።
በአምላክ ላይ እጁን ያነሳልና፤ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ለመገዳደርም ይሞክራል፤
ወፍራምና ጠንካራ ጋሻ አንግቦ፣በእልኸኝነት እየገሰገሰ ይመጣበታል፤
ፊቱ በስብ ተሸፍኗል፤ወገቡም በስብ ተወጥሯል፤