text
stringlengths
4
267
“ለመታጠቢያ እንዲሆን ከመዳብ ገንዳና ማስቀመጫውን ሥራ፤ በመገናኛ ድንኳኑና በመሠዊያው መካከል አስቀምጠው፤ ውኃም ጨምርበት።
አሮንና ወንዶች ልጆቹም እጃቸውንና እግራቸውን ይታጠቡበታል።
ወደ መገናኛ ድንኳኑ በሚገቡበት ወይም ለማገልገልና በእሳት የሚቀርብ መባ ለይሖዋ ለማቅረብ ወደ መሠዊያው በሚቀርቡበት ጊዜ እንዳይሞቱ በውኃ ይታጠባሉ።
እንዳይሞቱ እጃቸውንና እግራቸውን ይታጠቡ፤ ይህም ለእሱና ለዘሮቹ በትውልዶቻቸው ሁሉ ዘላለማዊ ሥርዓት ሆኖ ያገልግል።”
ይሖዋም እንዲህ በማለት ሙሴን ማነጋገሩን ቀጠለ፦
“አንተም ጥሩ መዓዛ ያላቸውን የሚከተሉትን ምርጥ ቅመሞች ውሰድ፦ 500 ሰቅል የረጋ ከርቤ፣ የዚህን ግማሽ ይኸውም 250 ሰቅል ጣፋጭ ቀረፋ፣ 250 ሰቅል ጥሩ መዓዛ ያለው ጠጅ ሣር፣
እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል መሠረት 500 ሰቅል ብርጉድ እንዲሁም አንድ ሂን የወይራ ዘይት።
ከእነዚህም ቅዱስ የቅብዓት ዘይት አዘጋጅ፤ በብልሃት የተቀመመ መሆን ይኖርበታል። ይህም ቅዱስ የቅብዓት ዘይት ይሆናል።
“አንተም የመገናኛ ድንኳኑንና የምሥክሩን ታቦት
እንዲሁም ጠረጴዛውንና ዕቃዎቹን በሙሉ፣ መቅረዙንና ዕቃዎቹን፣ የዕጣን መሠዊያውን፣
የሚቃጠል መባ የሚቀርብበትን መሠዊያና ዕቃዎቹን በሙሉ እንዲሁም የውኃ ገንዳውንና ማስቀመጫውን በዘይቱ ትቀባለህ።
እጅግ ቅዱስ እንዲሆኑም ቀድሳቸው። የሚነካቸው ማንኛውም ሰው ቅዱስ መሆን አለበት።
አንተም አሮንንና ወንዶች ልጆቹን ትቀባቸዋለህ፤ ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉኝም ትቀድሳቸዋለህ።
“አንተም ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ትነግራቸዋለህ፦ ‘በትውልዶቻችሁ ሁሉ ይህ ምንጊዜም ለእኔ ቅዱስ የቅብዓት ዘይት ይሆናል።
ይህ ማንም ሰው ሰውነቱን የሚቀባው አይደለም፤ እንዲሁም በተመሳሳይ መንገድ በመቀመም እንዲህ ያለ ቅባት ማዘጋጀት የለባችሁም። ይህ የተቀደሰ ነገር ነው። ለእናንተም ምንጊዜም የተቀደሰ ይሆናል።
ይህን የመሰለ ቅባት የሚሠራና ያልተፈቀደለትን ሰው የሚቀባ ማንኛውም ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረግ።’”
ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አንተም ጥሩ መዓዛ ካላቸው ቅመሞች ይኸውም ከሚንጠባጠብ ሙጫ፣ ከኦኒካ፣ ከሚሸት ሙጫ እንዲሁም ከንጹሕ ነጭ ዕጣን እኩል መጠን ውሰድ።
ከዚያም ዕጣን አድርገህ አዘጋጀው፤ ይህም ዕጣን በብልሃት የተቀመመ፣ ጨው የተጨመረበት፣ ንጹሕና ቅዱስ መሆን ይኖርበታል።
ከእሱም የተወሰነውን ወቅጠህ በማላም ራሴን ለአንተ በምገልጥበት በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ ባለው ምሥክር ፊት ታስቀምጠዋለህ። ይህም ለእናንተ እጅግ ቅዱስ መሆን ይኖርበታል።
በተመሳሳይ መንገድ የተቀመመ ዕጣን ለራስህ ማዘጋጀት የለብህም። ለይሖዋ የተቀደሰ እንደሆነ አድርገህ ልትመለከተው ይገባል።
በመዓዛው ለመደሰት ሲል ይህን የመሰለ ዕጣን የሚያዘጋጅ ማንኛውም ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረግ።”
ስለሆነም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ ፈርዖን ገብተህ እንዲህ በለው፦ ‘የዕብራውያን አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እንዲያገለግለኝ ሕዝቤን ልቀቅ።
እነሱን ለመልቀቅ እንቢተኛ የምትሆንና እንዳይሄዱ የምትከለክላቸው ከሆነ
የይሖዋ እጅ በመስክ ያሉትን ከብቶችህን ይመታል። በፈረሶች፣ በአህዮች፣ በግመሎች፣ በበሬዎች፣ በላሞችና በመንጎች ላይ አጥፊ መቅሰፍት ይወርዳል።
ይሖዋም በእስራኤል ከብቶችና በግብፅ ከብቶች መካከል ልዩነት እንዲኖር ያደርጋል፤ ከእስራኤላውያን ከብቶች መካከል አንድ እንኳ አይሞትም።”’”
ከዚህም በላይ ይሖዋ “በነገው ዕለት እኔ ይሖዋ በምድሪቱ ላይ ይህን አደርጋለሁ” በማለት ቀን ቆርጧል።
ይሖዋም በማግስቱ ይህን አደረገ፤ የግብፅ ከብት ሁሉ ይሞት ጀመር፤ ከእስራኤላውያን ከብቶች መካከል ግን አንድ እንኳ አልሞተም።
ፈርዖንም ሁኔታውን ሲያጣራ ከእስራኤላውያን ከብቶች መካከል አንድ እንኳ አለመሞቱን ተገነዘበ። ያም ሆኖ ግን የፈርዖን ልብ ደነደነ፤ ሕዝቡንም አለቀቀም።
ከዚያም ይሖዋ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ “ከሸክላ መተኮሻ ምድጃ እፍኝ ሙሉ ጥቀርሻ ውሰዱ፤ ሙሴም ጥቀርሻውን በፈርዖን ፊት ወደ ሰማይ ይበትነው።
ጥቀርሻውም በመላው የግብፅ ምድር ላይ አቧራ ይሆናል፤ ከዚያም በመላው የግብፅ ምድር ባለ ሰውና እንስሳ ላይ መግል የያዘ እባጭ ሆኖ ይወጣል።”
እነሱም ከሸክላ መተኮሻ ምድጃ ጥቀርሻ ወስደው ፈርዖን ፊት ቆሙ፤ ሙሴም ጥቀርሻውን ወደ ሰማይ በተነው፤ ጥቀርሻውም በሰውና በእንስሳ ላይ መግል የያዘ እባጭ ሆኖ ወጣ።
አስማተኞቹ ካህናት በእባጩ የተነሳ ሙሴ ፊት ሊቆሙ አልቻሉም፤ ምክንያቱም እባጩ በአስማተኞቹ ካህናትና በሁሉም ግብፃውያን ላይ ወጥቶ ነበር።
ሆኖም ይሖዋ የፈርዖን ልብ እንዲደነድን ፈቀደ፤ ፈርዖንም ልክ ይሖዋ ለሙሴ እንደነገረው እነሱን አልሰማቸውም።
ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በማለዳ ተነስተህ ፈርዖን ፊት ቁም፤ እንዲህም በለው፦ ‘የዕብራውያን አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እንዲያገለግለኝ ሕዝቤን ልቀቅ።
ምክንያቱም በመላው ምድር ላይ እንደ እኔ ያለ ማንም እንደሌለ እንድታውቅ ልብህን፣ አገልጋዮችህንና ሕዝብህን ለመምታት መቅሰፍቴን በሙሉ አሁን አወርዳለሁ።
እስካሁን እጄን ዘርግቼ አንተንም ሆነ ሕዝብህን አጥፊ በሆነ መቅሰፍት በመታኋችሁ ነበር፤ አንተም ከምድር ገጽ ተጠራርገህ በጠፋህ ነበር።
ሆኖም ኃይሌን እንዳሳይህና ስሜ በመላው ምድር እንዲታወጅ ስል በሕይወት አቆይቼሃለሁ።
ሕዝቤን አለቅም በማለት አሁንም በእነሱ ላይ እንደታበይክ ነህ?
እንግዲህ በነገው ዕለት በዚህ ሰዓት ገደማ ግብፅ ከተመሠረተችበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ሆኖ የማያውቅ እጅግ ታላቅ የበረዶ ውርጅብኝ አዘንባለሁ።
ስለዚህ አሁን መልእክት ልከህ በመስክ ላይ የተሰማሩትን ከብቶችህንና የአንተ የሆኑትን ሁሉ ወደ መጠለያ እንዲገቡ አድርግ። በመስክ የተገኘና ወደ ቤት ያልገባ ማንኛውም ሰውና እንስሳ በረዶው ይወርድበትና ይሞታል።”’”
ከፈርዖን አገልጋዮች መካከል የይሖዋን ቃል የፈሩ ሁሉ አገልጋዮቻቸውንና ከብቶቻቸውን በፍጥነት ወደ ቤት አስገቡ፤
ሆኖም የይሖዋን ቃል ከቁም ነገር ያልቆጠሩት ሁሉ አገልጋዮቻቸውንና ከብቶቻቸውን እዚያው መስክ ላይ እንዳሉ ተዉአቸው።
በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን “በመላው የግብፅ ምድር ላይ ይኸውም በሰው፣ በእንስሳና በግብፅ ምድር ላይ በበቀለው ተክል ሁሉ ላይ በረዶ እንዲወርድ እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ” አለው።
በመሆኑም ሙሴ በትሩን ወደ ሰማይ አነሳ፤ ይሖዋም ነጎድጓድና በረዶ ላከ፤ እሳትም በምድር ላይ ወረደ፤ ይሖዋ በግብፅ ምድር ላይ ያለማቋረጥ በረዶ እንዲወርድ አደረገ።
በረዶም ወረደ፤ በበረዶውም መካከል የእሳት ብልጭታ ነበር። በረዶውም እጅግ ከባድ ነበር፤ ግብፅ እንደ አገር ሆና ከተመሠረተችበት ጊዜ አንስቶ በዚያች ምድር ላይ እንዲህ ያለ በረዶ ተከስቶ አያውቅም።
በረዶው ከሰው አንስቶ እስከ እንስሳ ድረስ በግብፅ ምድር በመስክ ላይ የነበረውን ማንኛውንም ነገር መታ፤ ዕፀዋቱን ሁሉና በሜዳ ላይ ያለውን ዛፍ በሙሉ አወደመ።
በረዶ ያልወረደው እስራኤላውያን በሚኖሩበት በጎሸን ምድር ብቻ ነበር።
ስለሆነም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “አሁንስ በድያለሁ። ይሖዋ ጻድቅ ነው፤ ጥፋተኞቹ እኔና ሕዝቤ ነን።
አምላክ ያመጣው ነጎድጓድና በረዶ እንዲቆም ይሖዋን ለምኑልኝ። እኔም እናንተን ለመልቀቅ ፈቃደኛ እሆናለሁ፤ ከአሁን በኋላ እዚህ አትቆዩም።”
በመሆኑም ሙሴ እንዲህ አለው፦ “ልክ ከከተማዋ እንደወጣሁ እጆቼን በይሖዋ ፊት እዘረጋለሁ። ምድር የይሖዋ እንደሆነች እንድታውቅም ነጎድጓዱ ይቆማል፤ በረዶውም ከዚያ በኋላ አይወርድም።
ሆኖም አንተም ሆንክ አገልጋዮችህ ይህ ከሆነ በኋላም እንኳ ይሖዋ አምላክን እንደማትፈሩ አውቃለሁ።”
በዚህ ጊዜ ገብሱ አሽቶ፣ ተልባውም አብቦ ስለነበር ተልባውና ገብሱ ከጥቅም ውጭ ሆኑ።
ስንዴውና አጃው ግን ወቅታቸው ገና ስለነበር ጉዳት አልደረሰባቸውም።
ሙሴም ከፈርዖን ተለይቶ ከከተማዋ ወጣ፤ እጆቹንም በይሖዋ ፊት ዘረጋ፤ ነጎድጓዱና በረዶውም ቆመ፤ ዝናቡም በምድር ላይ መዝነቡን አቆመ።
ፈርዖንም ዝናቡ፣ በረዶውና ነጎድጓዱ መቆሙን ባየ ጊዜ እንደገና ኃጢአት ሠራ፤ እሱም ሆነ አገልጋዮቹ ልባቸውን አደነደኑ።
የፈርዖን ልብ ደነደነ፤ ልክ ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት እንደተናገረውም እስራኤላውያንን አለቀቀም።
እሱም የሚቃጠል መባ የሚቀርብበትን መሠዊያ ከግራር እንጨት ሠራ። ርዝመቱ አምስት ክንድ፣ ወርዱም አምስት ክንድ ሲሆን አራቱም ጎኖቹ እኩል ነበሩ፤ ከፍታው ደግሞ ሦስት ክንድ ነበር።
ከዚያም በአራቱ ማዕዘኖች ላይ ቀንዶቹን ሠራለት። ቀንዶቹም ከዚያው ወጥ ሆነው የተሠሩ ነበሩ። በመቀጠልም በመዳብ ለበጠው።
ከዚህ በኋላ የመሠዊያውን ዕቃዎች በሙሉ ይኸውም አመድ ማጠራቀሚያዎቹን፣ አካፋዎቹን፣ ሳህኖቹን፣ ሹካዎቹንና መኮስተሪያዎቹን ሠራ። ዕቃዎቹን በሙሉ ከመዳብ ሠራቸው።
በተጨማሪም ለመሠዊያው ከጠርዙ ወደ ታች ወረድ ብሎ ወደ መሃል አካባቢ እንደ መረብ ያለ የመዳብ ፍርግርግ ሠራለት።
መሎጊያዎቹን ለመያዝ የሚያገለግሉትንም አራት ቀለበቶች ከመዳብ ፍርግርጉ አጠገብ በአራቱ ማዕዘኖች ላይ ሠራ።
በኋላም መሎጊያዎቹን ከግራር እንጨት ሠርቶ በመዳብ ለበጣቸው።
ከዚያም መሠዊያውን ለመሸከም እንዲያገለግሉ መሎጊያዎቹን በመሠዊያው ጎኖች ላይ ባሉት ቀለበቶች ውስጥ አስገባቸው። መሠዊያውንም ባዶ ሣጥን አስመስሎ ከሳንቃዎች ሠራው።
ከዚያም የመዳቡን ገንዳና ከመዳብ የተሠራውን ማስቀመጫውን ሠራ፤ ለዚህም በመገናኛው ድንኳን መግቢያ ላይ በተደራጀ መልክ ያገለግሉ የነበሩትን ሴት አገልጋዮች መስተዋቶች ተጠቀመ።
ከዚያም ግቢውን ሠራ። በስተ ደቡብ በኩል ለሚገኘው፣ ፊቱ በደቡብ አቅጣጫ ላለው የግቢው ጎን በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ ርዝመታቸው 100 ክንድ የሆነ መጋረጃዎች ሠራ።
ከመዳብ የተሠሩ 20 ቋሚዎችና 20 መሰኪያዎች ነበሩ፤ በቋሚዎቹ ላይ ያሉት ማንጠልጠያዎችና ማያያዣዎቻቸው ደግሞ ከብር የተሠሩ ነበሩ።
በተጨማሪም በስተ ሰሜን በኩል ባለው ጎን ያሉት መጋረጃዎች ርዝመታቸው 100 ክንድ ነበር። ሃያዎቹ ቋሚዎቻቸውና 20ዎቹ መሰኪያዎቻቸው ከመዳብ የተሠሩ ነበሩ። በቋሚዎቹ ላይ ያሉት ማንጠልጠያዎችና ማያያዣዎቻቸው ደግሞ ከብር የተሠሩ ነበሩ።
በስተ ምዕራብ በኩል ባለው ጎን ያሉት መጋረጃዎች ግን ርዝመታቸው 50 ክንድ ነበር። አሥር ቋሚዎችና አሥር መሰኪያዎች ነበሩ፤ በቋሚዎቹ ላይ ያሉት ማንጠልጠያዎችና ማያያዣዎቻቸው ከብር የተሠሩ ነበሩ።
በስተ ምሥራቅ አቅጣጫ ይኸውም በፀሐይ መውጫ በኩል ያለው ጎን ርዝመቱ 50 ክንድ ነበር።
በአንደኛው በኩል ያሉት የመግቢያው መጋረጃዎች ርዝመታቸው 15 ክንድ ሲሆን ሦስት ቋሚዎችና ሦስት መሰኪያዎች ነበሯቸው።
በሌላኛው በኩል ያሉት የግቢው መግቢያ መጋረጃዎችም ርዝመታቸው 15 ክንድ ሲሆን ሦስት ቋሚዎችና ሦስት መሰኪያዎች ነበሯቸው።
በግቢው ዙሪያ ያሉት መጋረጃዎች በሙሉ በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ የተሠሩ ነበሩ።
የቋሚዎቹ መሰኪያዎች ከመዳብ የተሠሩ ነበሩ፤ በቋሚዎቹ ላይ ያሉት ማንጠልጠያዎችና ማያያዣዎቻቸው ከብር የተሠሩ ሲሆኑ አናታቸውም በብር የተለበጠ ነበር። የግቢው ቋሚዎች በሙሉ ከብር የተሠሩ ማያያዣዎች ነበሯቸው።
የግቢው መግቢያ መከለያ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግ እንዲሁም በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ የበፍታ ድር ተሸምኖ የተሠራ ነበር። ርዝመቱ 20 ክንድ ሲሆን ከፍታው ደግሞ ልክ እንደ ግቢው መጋረጃዎች 5 ክንድ ነበር።
አራቱ ቋሚዎቻቸውና አራቱ መሰኪያዎቻቸው ከመዳብ የተሠሩ ነበሩ። ማንጠልጠያዎቻቸው ከብር የተሠሩ ሲሆኑ አናታቸውና ማያያዣዎቻቸው ደግሞ በብር የተለበጡ ነበሩ።
የማደሪያ ድንኳኑና በግቢው ዙሪያ የሚገኙት ካስማዎች በሙሉ ከመዳብ የተሠሩ ነበሩ።
በሙሴ ትእዛዝ መሠረት ተቆጥረው የተመዘገቡት የማደሪያ ድንኳኑ ይኸውም የምሥክሩ የማደሪያ ድንኳን ዕቃዎች የሚከተሉት ናቸው፤ ይህን ያከናወኑት ሌዋውያኑ ሲሆኑ መሪያቸውም የካህኑ የአሮን ልጅ ኢታምር ነበር።
ከይሁዳ ነገድ የሆነው የሁር ልጅ የዖሪ ልጅ ባስልኤል ይሖዋ ሙሴን ያዘዘውን ሁሉ አደረገ።
ከእሱም ጋር ከዳን ነገድ የሆነው የአሂሳማክ ልጅ ኤልያብ ነበር፤ እሱም የእጅ ባለሙያና የጥልፍ ባለሙያ እንዲሁም በሰማያዊ ክር፣ በሐምራዊ ሱፍ፣ በደማቅ ቀይ ማግ እንዲሁም በጥሩ በፍታ የሚሸምን የሽመና ባለሙያ ነበር።
በአጠቃላይ በቅዱሱ ስፍራ ለተከናወነው ሥራ የዋለው ወርቅ በሙሉ መባ ሆኖ ከቀረበው ወርቅ ጋር ተመጣጣኝ ነበር፤ ይህም እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል 29 ታላንት ከ730 ሰቅል ነበር።
ከማኅበረሰቡ መካከል ከተመዘገቡት ሰዎች የተገኘው ብር ደግሞ እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል 100 ታላንት ከ1,775 ሰቅል ነበር።
ሃያ ዓመትና ከዚያ በላይ ሆኗቸው ከተመዘገቡት 603,550 ሰዎች መካከል የሆነ እያንዳንዱ ግለሰብ የሰጠው ግማሽ ሰቅል፣ እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል ግማሽ ሰቅል ነበር።
የቅዱሱን ስፍራ መሰኪያዎችና ለመጋረጃው ቋሚዎች የሚሆኑትን መሰኪያዎች ለመሥራት የዋለው 100 ታላንት ብር ነበር፤ 100 መሰኪያዎች 100 ታላንት ነበሩ፤ ይህም ለእያንዳንዱ መሰኪያ አንድ ታላንት ማለት ነው።
ለቋሚዎቹ ከ1,775 ሰቅል ብር ማንጠልጠያዎችን ሠራ፤ አናታቸውንም ከለበጠ በኋላ እርስ በርስ አያያዛቸው።
መባ ሆኖ የቀረበው መዳብ ደግሞ 70 ታላንት ከ2,400 ሰቅል ነበር።
በዚህም የመገናኛ ድንኳኑን መግቢያ መሰኪያዎች፣ የመዳብ መሠዊያውንና የመዳብ ፍርግርጉን እንዲሁም የመሠዊያውን ዕቃዎች በሙሉ ሠራ፤
እንዲሁም በግቢው ዙሪያ ያሉትን መሰኪያዎች፣ ለግቢው መግቢያ የሚሆኑትን መሰኪያዎች እንዲሁም የማደሪያ ድንኳኑን ካስማዎች በሙሉና በግቢው ዙሪያ ያሉትን የድንኳን ካስማዎች በሙሉ ሠራ።
ሙሴንም እንዲህ አለው፦ “አንተ፣ አሮን፣ ናዳብ፣ አቢሁና 70ዎቹ የእስራኤል ሽማግሌዎች ወደ ይሖዋ ውጡ፤ ከሩቅ ሆናችሁም ስገዱ።
ሙሴ ብቻውን ወደ ይሖዋ ይቅረብ፤ ሌሎቹ ግን መቅረብ የለባቸውም፤ ሕዝቡም ከእሱ ጋር መውጣት የለበትም።”
ከዚያም ሙሴ መጥቶ የይሖዋን ቃል ሁሉ እንዲሁም ድንጋጌዎቹን በሙሉ ለሕዝቡ ነገራቸው፤ ሕዝቡም ሁሉ “ይሖዋ የተናገረውን ቃል በሙሉ ለመፈጸም ፈቃደኞች ነን” ሲሉ በአንድ ድምፅ መለሱ።
ስለሆነም ሙሴ የይሖዋን ቃል ሁሉ በጽሑፍ አሰፈረ። በማለዳም ተነስቶ በተራራው ግርጌ መሠዊያና 12ቱን የእስራኤል ነገዶች የሚወክሉ 12 ዓምዶች ሠራ።
ከዚያም ወጣት እስራኤላውያን ወንዶችን ላከ፤ እነሱም የሚቃጠሉ መባዎችን አቀረቡ፤ እንዲሁም በሬዎችን የኅብረት መሥዋዕቶች አድርገው ለይሖዋ ሠዉ።
ሙሴም ከደሙ ግማሹን ወስዶ በሳህኖች ውስጥ አስቀመጠው፤ ግማሹን ደም ደግሞ በመሠዊያው ላይ ረጨው።
ከዚያም የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ ወስዶ ድምፁን ከፍ በማድረግ ለሕዝቡ አነበበ። ሕዝቡም “ይሖዋ የተናገረውን ሁሉ ለመፈጸምና ለመታዘዝ ፈቃደኞች ነን” አሉ።
በመሆኑም ሙሴ ደሙን ወስዶ በሕዝቡ ላይ ረጨው፤ እንዲህም አለ፦ “በእነዚህ ቃላት መሠረት ይሖዋ ከእናንተ ጋር የገባው ቃል ኪዳን ደም ይህ ነው።”
ሙሴ፣ አሮን፣ ናዳብ፣ አቢሁና 70ዎቹ የእስራኤል ሽማግሌዎች ወደ ላይ ወጡ፤
የእስራኤልንም አምላክ አዩ። ከእግሩም ሥር እንደ ሰማይ የጠራ የሰንፔር ንጣፍ የሚመስል ነገር ነበር።
እሱም በእስራኤል አለቆች ላይ ጉዳት አላደረሰባቸውም፤ እነሱም እውነተኛውን አምላክ በራእይ ተመለከቱ፤ በሉ፣ ጠጡም።
በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ እኔ ወደ ተራራው ውጣና በዚያ ቆይ። ለሕዝቡ መመሪያ እንዲሆን እኔ የጻፍኩትን ሕግና ትእዛዝ የያዙትን የድንጋይ ጽላቶች እሰጥሃለሁ።”
በመሆኑም ሙሴ ከአገልጋዩ ከኢያሱ ጋር ተነስቶ ወደ እውነተኛው አምላክ ተራራ ወጣ።