text
stringlengths
4
267
“የሰለጰአድ ሴቶች ልጆች ትክክል ናቸው። በአባታቸው ወንድሞች መካከል ርስታቸውን ውርስ አድርገህ ልትሰጣቸው ይገባል፤ የአባታቸውም ውርስ ለእነሱ እንዲተላለፍ ማድረግ አለብህ።
እስራኤላውያንንም እንዲህ በላቸው፦ ‘አንድ ሰው ወንድ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት ውርሱ ለሴት ልጆቹ እንዲተላለፍ ማድረግ አለባችሁ።
ሴት ልጅ ከሌለው ደግሞ ውርሱን ለወንድሞቹ ትሰጣላችሁ።
ወንድሞች ከሌሉት ውርሱን ለአባቱ ወንድሞች ትሰጣላችሁ።
አባቱ ወንድሞች ከሌሉት ውርሱን ከቤተሰቡ መካከል ቅርብ ለሆነው የሥጋ ዘመዱ ትሰጣላችሁ፤ እሱም ርስት አድርጎ ይወስደዋል። ይህም ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ለእስራኤላውያን የተደነገገ ደንብ ሆኖ ያገለግላል።’”
ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደዚህ ወደ አባሪም ተራራ ውጣና ለእስራኤላውያን የምሰጠውን ምድር ተመልከት።
ካየኸውም በኋላ እንደ ወንድምህ እንደ አሮን አንተም ወደ ወገኖችህ ትሰበሰባለህ፤
ምክንያቱም ማኅበረሰቡ በጺን ምድረ በዳ ከእኔ ጋር በተጣላ ጊዜ ከውኃዎቹ ጋር በተያያዘ በፊታቸው ሳትቀድሱኝ በመቅረታችሁ ትእዛዜን ተላልፋችኋል። እነዚህም በጺን ምድረ በዳ በቃዴስ የሚገኙት የመሪባ ውኃዎች ናቸው።
ከዚያም ሙሴ ይሖዋን እንዲህ አለው፦
“የሰው ሁሉ መንፈስ አምላክ የሆነው ይሖዋ በማኅበረሰቡ ላይ አንድ ሰው ይሹም፤
እሱም የይሖዋ ማኅበረሰብ እረኛ እንደሌላቸው በጎች እንዳይሆን በፊታቸው የሚወጣና የሚገባ እንዲሁም እነሱን መርቶ የሚያወጣና የሚያስገባ ይሆናል።”
በመሆኑም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “መንፈስ ያለበትን የነዌን ልጅ ኢያሱን ወስደህ እጅህን ጫንበት።
ከዚያም በካህኑ በአልዓዛርና በመላው ማኅበረሰብ ፊት አቁመው፤ በፊታቸውም ሹመው።
መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ እንዲሰማውም ከሥልጣንህ የተወሰነውን ስጠው።
እሱም በኡሪም አማካኝነት የይሖዋን ፍርድ በሚጠይቅለት በካህኑ በአልዓዛር ፊት ይቆማል። እሱም ሆነ ከእሱ ጋር ያሉት እስራኤላውያን እንዲሁም መላው ማኅበረሰብ በእሱ ትእዛዝ ይወጣሉ፤ በእሱ ትእዛዝ ይገባሉ።”
በመሆኑም ሙሴ ልክ ይሖዋ እንዳዘዘው አደረገ። ኢያሱንም ወስዶ በካህኑ በአልዓዛርና በመላው ማኅበረሰብ ፊት አቆመው፤
ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት በተናገረውም መሠረት እጆቹን በእሱ ላይ በመጫን ሾመው።
ይሖዋ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦
“እስራኤላውያን ሦስት ነገዶችን ላቀፈው ምድባቸው በተሰጠው ቦታ ይስፈሩ፤ እያንዳንዱም ሰው ለአባቶቹ ቤት በቆመው ዓርማ አጠገብ ይስፈር። ፊታቸውን ወደ መገናኛ ድንኳኑ አድርገው ዙሪያውን ይስፈሩ።
“በስተ ምሥራቅ ፀሐይ በምትወጣበት አቅጣጫ በየምድቡ የሚሰፍረው ሦስት ነገዶችን ያቀፈው የይሁዳ ምድብ ይሆናል፤ የይሁዳ ልጆች አለቃ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን ነው።
በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 74,600 ናቸው።
ከእሱም ቀጥሎ የሚሰፍረው የይሳኮር ነገድ ይሆናል፤ የይሳኮር ልጆች አለቃ የጹአር ልጅ ናትናኤል ነው።
በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 54,400 ናቸው።
ከዚያ ቀጥሎ የዛብሎን ነገድ ይስፈር፤ የዛብሎን ልጆች አለቃ የሄሎን ልጅ ኤልያብ ነው።
በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 57,400 ናቸው።
“በይሁዳ ምድብ በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡት በአጠቃላይ 186,400 ናቸው። መጀመሪያ ድንኳናቸውን ነቅለው የሚነሱት እነሱ ይሆናሉ።
“ሦስት ነገዶችን ያቀፈው የሮቤል ምድብ በየምድቡ በመሆን በስተ ደቡብ አቅጣጫ ይስፈር፤ የሮቤል ልጆች አለቃ የሸደኡር ልጅ ኤሊጹር ነው።
በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 46,500 ናቸው።
ከእሱ ቀጥሎ የሚሰፍረው የስምዖን ነገድ ይሆናል፤ የስምዖን ልጆች አለቃ የጹሪሻዳይ ልጅ ሸሉሚኤል ነው።
በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 59,300 ናቸው።
ከዚያ ቀጥሎ የጋድ ነገድ ይስፈር፤ የጋድ ልጆች አለቃ የረኡዔል ልጅ ኤሊያሳፍ ነው።
በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 45,650 ናቸው።
“በሮቤል ምድብ በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡት በአጠቃላይ 151,450 ናቸው፤ በሁለተኛ ደረጃ ድንኳናቸውን ነቅለው የሚነሱት እነሱ ናቸው።
“የመገናኛ ድንኳኑ ከቦታ ወደ ቦታ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ የሌዋውያኑ ሰፈር በሌሎቹ ሰፈሮች መሃል መሆን ይኖርበታል። “እነሱም ልክ በሰፈሩበት ሁኔታ እያንዳንዳቸው ቦታቸውን ጠብቀው ሦስት ነገድ ባቀፈው ምድባቸው መሠረት መጓዝ ይኖርባቸዋል።
“ሦስት ነገዶችን ያቀፈው የኤፍሬም ምድብ በየምድቡ በመሆን በስተ ምዕራብ አቅጣጫ ይስፈር፤ የኤፍሬም ልጆች አለቃ የአሚሁድ ልጅ ኤሊሻማ ነው።
በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 40,500 ናቸው።
ከእሱም ቀጥሎ የምናሴ ነገድ ይስፈር፤ የምናሴ ልጆች አለቃ የፐዳጹር ልጅ ገማልያል ነው።
በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 32,200 ናቸው።
ከዚያ ቀጥሎ የቢንያም ነገድ ይስፈር፤ የቢንያም ልጆች አለቃ የጊድኦኒ ልጅ አቢዳን ነው።
በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 35,400 ናቸው።
“በኤፍሬም ምድብ በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡት በአጠቃላይ 108,100 ናቸው፤ በሦስተኛ ደረጃ ድንኳናቸውን ነቅለው የሚነሱት እነሱ ናቸው።
“ሦስት ነገዶችን ያቀፈው የዳን ምድብ በየምድቡ በመሆን በስተ ሰሜን አቅጣጫ ይስፈር፤ የዳን ልጆች አለቃ የአሚሻዳይ ልጅ አሂዔዜር ነው።
በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 62,700 ናቸው።
ከእሱም ቀጥሎ የሚሰፍረው የአሴር ነገድ ይሆናል፤ የአሴር ልጆች አለቃ የኦክራን ልጅ ፓጊኤል ነው።
በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 41,500 ናቸው።
ከዚያ ቀጥሎ የንፍታሌም ነገድ ይስፈር፤ የንፍታሌም ልጆች አለቃ የኤናን ልጅ አሂራ ነው።
በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 53,400 ናቸው።
“በዳን ምድብ የተመዘገቡት በአጠቃላይ 157,600 ናቸው። ሦስት ነገዶችን ባቀፈው ምድባቸው መሠረት መጨረሻ ላይ ድንኳናቸውን ነቅለው የሚነሱት እነሱ ናቸው።”
በአባቶቻቸው ቤት መሠረት የተመዘገቡት እስራኤላውያን እነዚህ ነበሩ፤ ወደ ሠራዊቱ ለመቀላቀል በሰፈሩ ውስጥ የተመዘገቡት በአጠቃላይ 603,550 ነበሩ።
ሌዋውያኑ ግን ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ከሌሎቹ እስራኤላውያን ጋር አልተመዘገቡም።
እስራኤላውያንም ይሖዋ ሙሴን ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ። እያንዳንዳቸው በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት በመሆን ሦስት ነገዶችን ባቀፈው ምድባቸው መሠረት የሰፈሩትም ሆነ ድንኳናቸውን ነቅለው የተነሱት በዚህ መንገድ ነው።
ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦
“ሁለት መለከቶችን ለራስህ ሥራ፤ ወጥ ከሆነ ብር ጠፍጥፈህ ሥራቸው፤ መለከቶቹንም ማኅበረሰቡን ለመሰብሰብና ሕዝቡ ከሰፈረባቸው ቦታዎች ተነስቶ እንዲሄድ ምልክት ለመስጠት ተጠቀምባቸው።
ሁለቱም መለከቶች ሲነፉ መላው ማኅበረሰብ በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ ወደ አንተ ይሰብሰብ።
አንዱ መለከት ብቻ ከተነፋ ግን የእስራኤል የሺህ አለቆች ብቻ ወደ አንተ ይሰብሰቡ።
“ድምፁን እያለዋወጣችሁ መለከቱን ስትነፉ በስተ ምሥራቅ የሰፈሩት ተነስተው ይጓዙ።
ለሁለተኛ ጊዜ ድምፁን እያለዋወጣችሁ መለከቱን ስትነፉ በስተ ደቡብ የሰፈሩት ተነስተው ይጓዙ። ከመካከላቸው አንዱ ምድብ ተነስቶ በተጓዘ ቁጥር መለከቱን በዚህ መንገድ ይንፉ።
“ጉባኤውን አንድ ላይ በምትሰበስቡበት ጊዜ መለከቶቹን መንፋት ይኖርባችኋል፤ በዚህ ጊዜ ግን ድምፁን እያለዋወጣችሁ መንፋት የለባችሁም።
ካህናት የሆኑት የአሮን ወንዶች ልጆች መለከቶቹን ይንፉ፤ መለከቶቹን በዚህ መንገድ መጠቀም በትውልዶቻችሁ ሁሉ ለእናንተ ዘላቂ ደንብ ሆኖ ያገለግላል።
“ግፍ ከሚፈጽምባችሁ ጨቋኝ ጠላት ጋር በምድራችሁ ጦርነት ብትገጥሙ በመለከቶቹ አማካኝነት የክተት ጥሪ አሰሙ፤ አምላካችሁ ይሖዋም ያስባችኋል፤ ከጠላቶቻችሁም ያድናችኋል።
“እንዲሁም በደስታችሁ ወቅት ይኸውም በበዓላት ወቅቶችና የወር መባቻን ስታከብሩ በሚቃጠሉ መባዎቻችሁ እንዲሁም በኅብረት መሥዋዕቶቻችሁ ላይ መለከቶቹን ንፉ፤ እነሱም በአምላካችሁ ፊት ለእናንተ እንደ መታሰቢያ ሆነው ያገለግላሉ። እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።”
በሁለተኛው ዓመት ሁለተኛ ወር፣ ከወሩም በ20ኛው ቀን ደመናው ከምሥክሩ የማደሪያ ድንኳን ላይ ተነሳ።
እስራኤላውያንም በወጣላቸው የጉዞ ቅደም ተከተል መሠረት ከሲና ምድረ በዳ ተነስተው መጓዝ ጀመሩ፤ ደመናውም በፋራን ምድረ በዳ ቆመ።
ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ተነስተው ሲጓዙ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ነበር።
ሦስት ነገዶችን ያቀፈው የይሁዳ ልጆች ምድብ በየምድቡ በመሆን በመጀመሪያ ተነስቶ ተጓዘ፤ የምድቡም አለቃ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን ነበር።
የይሳኮር ልጆች ነገድ ምድብ አለቃም የጹአር ልጅ ናትናኤል ነበር።
የዛብሎን ልጆች ነገድ ምድብ አለቃ የሄሎን ልጅ ኤልያብ ነበር።
የማደሪያ ድንኳኑ በተነቀለም ጊዜ የማደሪያ ድንኳኑን የሚሸከሙት የጌድሶን ወንዶች ልጆችና የሜራሪ ወንዶች ልጆች ተነስተው ተጓዙ።
ከዚያም ሦስት ነገዶችን ያቀፈው የሮቤል ምድብ በየምድቡ በመሆን ተነስቶ ተጓዘ፤ የምድቡም አለቃ የሸደኡር ልጅ ኤሊጹር ነበር።
የስምዖን ልጆች ነገድ ምድብ አለቃ የጹሪሻዳይ ልጅ ሸሉሚኤል ነበር።
የጋድ ልጆች ነገድ ምድብ አለቃ የደኡዔል ልጅ ኤሊያሳፍ ነበር።
ከዚያም የመቅደሱን ዕቃዎች የሚሸከሙት ቀአታውያን ተነስተው ተጓዙ። እነሱ በሚደርሱበት ጊዜ የማደሪያ ድንኳኑ ተተክሎ ይቆያል።
ቀጥሎም ሦስት ነገዶችን ያቀፈው የኤፍሬም ምድብ በየምድቡ በመሆን ተነስቶ ተጓዘ፤ የምድቡም አለቃ የአሚሁድ ልጅ ኤሊሻማ ነበር።
የምናሴ ልጆች ነገድ ምድብ አለቃ የፐዳጹር ልጅ ገማልያል ነበር።
የቢንያም ልጆች ነገድ ምድብ አለቃ የጊድኦኒ ልጅ አቢዳን ነበር።
ከዚያም ሦስት ነገዶችን ያቀፈው የዳን ልጆች ምድብ ለሁሉም ምድቦች የኋላ ደጀን በመሆን በየምድቡ ተነስቶ ተጓዘ፤ የሠራዊቱም አለቃ የአሚሻዳይ ልጅ አሂዔዜር ነበር።
የአሴር ልጆች ነገድ ምድብ አለቃ የኦክራን ልጅ ፓጊኤል ነበር።
የንፍታሌም ልጆች ነገድ ምድብ አለቃ የኤናን ልጅ አሂራ ነበር።
እስራኤላውያን በየምድባቸው በመሆን ተነስተው የሚጓዙበት የጉዞ ቅደም ተከተል ይህ ነበር።
ከዚያም ሙሴ የአማቱን የምድያማዊውን የረኡዔልን ልጅ ሆባብን እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ እኛ ይሖዋ ‘ለእናንተ እሰጣችኋለሁ’ ወዳለን ምድር ተነስተን መጓዛችን ነው። አንተም ከእኛ ጋር ና፤ ይሖዋ ለእስራኤል መልካም ነገር ለማድረግ ቃል ስለገባ እኛም መልካም ነገር እናደርግልሃለን።”
እሱ ግን “አብሬያችሁ አልሄድም። እኔ ወደ አገሬና ወደ ዘመዶቼ እመለሳለሁ” አለው።
በዚህ ጊዜ እንዲህ አለው፦ “በምድረ በዳው የት መስፈር እንዳለብን ስለምታውቅ እባክህ ትተኸን አትሂድ፤ መንገድም ልትመራን ትችላለህ።
ከእኛ ጋር የምትሄድ ከሆነ ይሖዋ የሚያደርግልንን መልካም ነገር ሁሉ እኛም በእርግጥ ለአንተ እናደርግልሃለን።”
በመሆኑም የሦስት ቀን መንገድ ለመጓዝ ከይሖዋ ተራራ ተነስተው ጉዞ ጀመሩ፤ የሦስት ቀኑን ጉዞ በሚጓዙበት ጊዜም የይሖዋ የቃል ኪዳን ታቦት ለእነሱ የማረፊያ ቦታ ለመፈለግ ከፊት ከፊታቸው ይሄድ ነበር።
ከሰፈሩበት ቦታ በሚነሱበት ጊዜ የይሖዋ ደመና ቀን ቀን በላያቸው ይሆን ነበር።
ታቦቱ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ ሁሉ ሙሴ “ይሖዋ ሆይ፣ ተነስ፤ ጠላቶችህ ይበታተኑ፤ የሚጠሉህም ሁሉ ከፊትህ ይሽሹ” ይል ነበር።
ታቦቱ በሚያርፍበትም ጊዜ “ይሖዋ ሆይ፣ በሺዎች ወደሚቆጠሩት ስፍር ቁጥር የሌላቸው እስራኤላውያን ተመለስ” ይል ነበር።
ከዚያም የሌዊ ልጅ፣ የቀአት ልጅ፣ የይጽሃር ልጅ ቆሬ ከሮቤል ልጆች አንዱ ከሆነው ከኤልያብ ልጆች ከዳታንና ከአቤሮን እንዲሁም ከሮቤል ልጆች አንዱ ከሆነው ከፐሌት ልጅ ከኦን ጋር በመሆን ተነሳ።
እነሱም ከማኅበረሰቡ አለቆች ይኸውም ከጉባኤው መካከል ከተመረጡት ታዋቂ የሆኑ 250 እስራኤላውያን ወንዶች ጋር በማበር በሙሴ ላይ ተነሱ።
እነሱም ሙሴንና አሮንን ለመቃወም ተሰብስበው መጡ፤ እንዲህም አሏቸው፦ “ምነው፣ አላበዛችሁትም እንዴ! መላው ማኅበረሰብ እኮ ቅዱስ ነው፤ ሁሉም ቅዱስ ናቸው፤ ይሖዋም በመካከላቸው ነው። ታዲያ በይሖዋ ጉባኤ ላይ ራሳችሁን ከፍ ከፍ የምታደርጉት ለምንድን ነው?”
ሙሴ ይህን ሲሰማ ወዲያውኑ በግንባሩ ተደፋ።
ከዚያም ቆሬንና ግብረ አበሮቹን ሁሉ እንዲህ አላቸው፦ “ጠዋት ላይ ይሖዋ የእሱ የሆነውን፣ ቅዱስ የሆነውንና ወደ እሱ መቅረብ የሚችለውን ሰው ያሳውቃል፤ እሱ የመረጠውም ሰው ወደ እሱ ይቀርባል።
ስለዚህ እንዲህ አድርጉ፦ ቆሬ፣ አንተም ሆንክ ግብረ አበሮችህ በሙሉ የዕጣን ማጨሻዎች ውሰዱ፤
ከዚያም በነገው ዕለት እሳት ካደረጋችሁባቸው በኋላ በይሖዋ ፊት ዕጣን ጨምሩባቸው፤ ይሖዋ የሚመርጠውም ሰው፣ እሱ ቅዱስ ይሆናል። እናንተ የሌዊ ልጆች፣ በጣም አብዝታችሁታል!”
ከዚያም ሙሴ ቆሬን እንዲህ አለው፦ “እናንተ የሌዊ ልጆች፣ እባካችሁ አዳምጡ።
የእስራኤል አምላክ እናንተን ከእስራኤል ማኅበረሰብ መለየቱ እንዲሁም በይሖዋ የማደሪያ ድንኳን የሚከናወነውን አገልግሎት ትፈጽሙና በማኅበረሰቡ ፊት ቆማችሁ እነሱን ታገለግሉ ዘንድ ወደ እሱ እንድትቀርቡ መፍቀዱ እንደ ቀላል ነገር የሚታይ ነው?
ደግሞስ አንተንና የሌዊ ልጆች የሆኑትን ወንድሞችህን በሙሉ ወደ እሱ እንድትቀርቡ ማድረጉ ቀላል ነገር ነው? ታዲያ የክህነት አገልግሎቱንም ለመጠቅለል መሞከር ይገባችኋል?
ስለዚህ አንተም ሆንክ አብረውህ የተሰበሰቡት ግብረ አበሮችህ በሙሉ ይሖዋን እየተቃወማችሁ ነው። በአሮን ላይ የምታጉረመርሙት እሱ ምን ስለሆነ ነው?”
ከዚያም ሙሴ የኤልያብን ልጆች ዳታንንና አቤሮንን አስጠራቸው፤ እነሱ ግን እንዲህ አሉ፦ “አንመጣም!
በምድረ በዳ ልትገድለን ወተትና ማር ከምታፈሰው ምድር ያወጣኸን አይበቃህም? አሁን ደግሞ በእኛ ላይ ፈላጭ ቆራጭ ልትሆን ያምርሃል?