text
stringlengths
4
267
ከዚያም ይህን ምሳሌያዊ አባባል ተናገረ፦ “የሞዓብ ንጉሥ ባላቅ ከአራም፣ከምሥራቅ ተራሮች አመጣኝ፤ ‘ና፣ ያዕቆብን እርገምልኝ። አዎ ና፣ እስራኤልን አውግዝልኝ’ አለኝ።
አምላክ ያልረገመውን እኔ እንዴት ልረግም እችላለሁ? ይሖዋ ያላወገዘውንስ እኔ እንዴት ላወግዝ እችላለሁ?
ከዓለቶቹ አናት ላይ ሆኜ አያቸዋለሁ፤ከኮረብቶቹም ላይ ሆኜ እመለከታቸዋለሁ። በዚያ እንደ አንድ ሕዝብ ብቻቸውን ሰፍረዋል፤ከሌሎች ብሔራት እንደ አንዱ አድርገው ራሳቸውን አይቆጥሩም።
ከብዛቱ የተነሳ እንደ አፈር የሆነውን ያዕቆብን ማን ሊቆጥረው ይችላል?የእስራኤልንስ ሩብ ማን ይቆጥረዋል? የቅኖች ዓይነት አሟሟት ልሙት፤መጨረሻዬም እንደ እነሱ ይሁን።”
ባላቅም በለዓምን እንዲህ አለው፦ “እንዴት እንዲህ ታደርገኛለህ? እኔ እኮ ያመጣሁህ ጠላቶቼን እንድትረግምልኝ ነው፤ አንተ ግን ባረክሃቸው እንጂ ምንም አልፈየድክልኝም።”
እሱም መልሶ “እኔ መናገር ያለብኝ ይሖዋ በአፌ ላይ ያስቀመጠውን ብቻ አይደለም?” አለ።
ከዚያም ባላቅ እንዲህ አለው፦ “እባክህ፣ እነሱን ማየት ወደምትችልበት ሌላ ቦታ አብረን እንሂድ። እርግጥ ሁሉንም አታያቸውም፤ የምታያቸው በከፊል ብቻ ነው። እዚያ ሆነህ እርገምልኝ።”
እሱም በጲስጋ አናት ላይ ወደሚገኘው የጾፊም ሜዳ ወሰደው፤ በዚያም ሰባት መሠዊያዎችን ሠርቶ በእያንዳንዱ መሠዊያ ላይ አንድ በሬና አንድ አውራ በግ አቀረበ።
በለዓምም ባላቅን “እኔ ከእሱ ጋር ለመገናኘት ወደዚያ ስሄድ አንተ እዚሁ የሚቃጠለው መባህ አጠገብ ቆይ” አለው።
ይሖዋም ከበለዓም ጋር ተገናኘ፤ በአፉም ላይ ይህን ቃል አስቀመጠ፦ “ወደ ባላቅ ተመለስና እንዲህ ብለህ ንገረው።”
በመሆኑም በለዓም ወደ ባላቅ ተመለሰ፤ ባላቅንም በሚቃጠለው መባው አጠገብ ሲጠብቀው አገኘው፤ የሞዓብ መኳንንትም ከእሱ ጋር ነበሩ። ከዚያም ባላቅ “ለመሆኑ ይሖዋ ምን አለ?” ሲል ጠየቀው።
በለዓምም ይህን ምሳሌያዊ አባባል ተናገረ፦ “ባላቅ ተነስ፤ አዳምጥ። የሴፎር ልጅ ሆይ፣ ጆሮህን ስጠኝ።
አምላክ እንደ ሰው አይዋሽም፤እንደ ሰው ልጅም ሐሳቡን አይለውጥም። እሱ ያለውን አያደርገውም? የተናገረውንስ አይፈጽመውም?
እንግዲህ የእኔ ተልእኮ መባረክ ነው፤እሱ እንደሆነ ባርኳል፤ እኔ ደግሞ ልለውጠው አልችልም።
ያዕቆብን ለማጥቃት የታሰበን ማንኛውንም አስማታዊ ኃይል ዝም ብሎ አያልፍም፤በእስራኤል ላይ ምንም ዓይነት ችግር እንዲደርስ አይፈቅድም። አምላኩ ይሖዋ ከእነሱ ጋር ነው፤በመካከላቸውም እንደ ንጉሥ ከፍ ባለ ድምፅ ይወደሳል።
አምላክ ከግብፅ አውጥቷቸዋል። እሱም ለእነሱ ልክ እንደ ጎሽ ቀንዶች ነው።
በያዕቆብ ላይ የሚሠራ ምንም ዓይነት ድግምት የለምና፤በእስራኤልም ላይ የሚሠራ ምንም ዓይነት ሟርት የለም። በዚህ ጊዜ ስለ ያዕቆብና ስለ እስራኤል ‘አምላክ ያደረገውን ተመልከቱ!’ ይባላል።
ልክ እንደ አንበሳ የሚነሳው ሕዝብ ይህ ነው፤እሱም እንደ አንበሳ ተነስቶ ይቆማል። ያደነውን እስኪበላ፣የተገደሉትንም ደማቸውን እስኪጠጣ ድረስ አይተኛም።”
ከዚያም ባላቅ በለዓምን “እንግዲያው ልትረግመው ካልቻልክ ልትባርከውም አይገባም” አለው።
በለዓምም መልሶ ባላቅን “‘እኔ የማደርገው ይሖዋ የሚናገረውን ብቻ ነው’ ብዬህ አልነበረም?” አለው።
ባላቅም በለዓምን እንዲህ አለው፦ “እባክህ ና፤ እስቲ አሁንም ወደ ሌላ ቦታ ልውሰድህ። ምናልባትም እውነተኛው አምላክ እዚያ ሆነህ እሱን እንድትረግምልኝ ይፈቅድ ይሆናል።”
ስለዚህ ባላቅ በለዓምን፣ የሺሞንን ፊት ለፊት ማየት ወደሚቻልበት ወደ ፌጎር አናት ወሰደው።
ከዚያም በለዓም ባላቅን “እዚህ ቦታ ላይ ሰባት መሠዊያዎች ሥራልኝ፤ እንዲሁም ሰባት በሬዎችና ሰባት አውራ በጎች አዘጋጅልኝ” አለው።
ባላቅም በለዓም እንዳለው አደረገ፤ ከዚያም በእያንዳንዱ መሠዊያ ላይ አንድ በሬና አንድ አውራ በግ አቀረበ።
ይሖዋ ሙሴን በኢያሪኮ በሚገኘው በዮርዳኖስ አጠገብ ባለው የሞዓብ በረሃማ ሜዳ ላይ እንዲህ አለው፦
“እስራኤላውያንን ከሚወርሱት ርስት ላይ ለሌዋውያኑ መኖሪያ የሚሆኑ ከተሞችን እንዲሰጧቸው እዘዛቸው፤ በከተሞቹም ዙሪያ ያለውን የግጦሽ መሬት ለሌዋውያኑ መስጠት አለባቸው።
ከተሞቹ ለእነሱ መኖሪያ፣ የግጦሽ ቦታዎቹ ደግሞ ለከብቶቻቸውና ለዕቃዎቻቸው እንዲሁም ለሌሎች እንስሶቻቸው ይሆናሉ።
ለሌዋውያኑ የምትሰጧቸው የከተሞቹ የግጦሽ ቦታዎች ከከተማው ቅጥር በሁሉም አቅጣጫ 1,000 ክንድ ይሆናል።
ከተማውን መካከል ላይ በማድረግ ከከተማው ውጭ በምሥራቅ በኩል 2,000 ክንድ፣ በደቡብ በኩል 2,000 ክንድ፣ በምዕራብ በኩል 2,000 ክንድ እንዲሁም በሰሜን በኩል 2,000 ክንድ ለኩ። እነዚህም የከተሞቻቸው የግጦሽ መሬት ይሆናሉ።
“ለሌዋውያኑ የምትሰጧቸው ከተሞች ነፍስ ያጠፋ ሰው ሸሽቶ የሚሸሸግባቸውን 6 የመማጸኛ ከተሞችና ሌሎች 42 ከተሞችን ነው።
በጠቅላላ 48 ከተሞችን ከነግጦሽ መሬታቸው ለሌዋውያኑ ትሰጧቸዋላችሁ።
ከተሞቹን የምትሰጧቸው ከእስራኤላውያን ርስት ላይ ወስዳችሁ ነው። ተለቅ ካለው ቡድን ላይ ብዙ ትወስዳላችሁ፤ አነስ ካለው ቡድን ላይ ደግሞ ጥቂት ትወስዳላችሁ። እያንዳንዱ ቡድን በወረሰው ርስት መጠን ካሉት ከተሞች ላይ የተወሰኑትን ለሌዋውያኑ መስጠት ይኖርበታል።”
ይሖዋ በመቀጠል ሙሴን እንዲህ አለው፦
“እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፦ ‘እንግዲህ ወደ ከነአን ምድር ለመግባት ዮርዳኖስን ልትሻገሩ ነው።
ሳያስበው ሰው የገደለ ሰው ሸሽቶ የሚጠጋባቸው አመቺ የሆኑ የመማጸኛ ከተሞችን ለራሳችሁ ምረጡ።
እነዚህ ከተሞች ነፍስ ያጠፋው ሰው በማኅበረሰቡ ፊት ለፍርድ ከመቅረቡ በፊት እንዳይሞት ከደም ተበቃዩ የሚሸሸግባቸው ከተሞች ይሆኑላችኋል።
እናንተ የምትሰጧቸው ስድስቱ የመማጸኛ ከተሞች ለዚህ ዓላማ ያገለግላሉ።
የመማጸኛ ከተሞች ሆነው እንዲያገለግሉ ከዮርዳኖስ ወዲህ ሦስት ከተሞችን፣ በከነአን ምድር ደግሞ ሦስት ከተሞችን ትሰጣላችሁ።
እነዚህ ስድስት ከተሞች ለእስራኤላውያንም ሆነ ለባዕድ አገር ሰው አሊያም በመካከላቸው ለሚኖር ሰፋሪ ሳያስበው ሰው የገደለ ማንኛውም ሰው ሸሽቶ የሚጠጋባቸው ከተሞች ሆነው ያገለግላሉ።
“‘ሆኖም ሰውየው ግለሰቡን በብረት መሣሪያ ቢመታውና ቢገድለው ይህ ሰው ነፍሰ ገዳይ ነው። ነፍሰ ገዳዩ ያለምንም ጥርጥር መገደል አለበት።
ሰውየው ግለሰቡን ሊገድለው በሚችል ድንጋይ ቢመታውና ቢገድለው ይህ ሰው ነፍሰ ገዳይ ነው። ነፍሰ ገዳዩ ያለምንም ጥርጥር መገደል አለበት።
ሰውየው ግለሰቡን ሊገድለው በሚችል ከእንጨት የተሠራ መሣሪያ ቢመታውና ቢገድለው ይህ ሰው ነፍሰ ገዳይ ነው። ነፍሰ ገዳዩ ያለምንም ጥርጥር መገደል አለበት።
“‘ነፍሰ ገዳዩን መግደል ያለበት ደም ተበቃዩ ይሆናል። ባገኘው ጊዜ እሱ ራሱ ይግደለው።
አንድ ሰው ሌላውን በጥላቻ ተገፋፍቶ ቢገፈትረው ወይም ተንኮል አስቦ የሆነ ነገር ቢወረውርበትና ግለሰቡ ቢሞት
አሊያም በጥላቻ ተነሳስቶ በእጁ ቢመታውና ቢሞት መቺው ያለምንም ጥርጥር ይገደላል። እሱ ነፍሰ ገዳይ ነው። ደም ተበቃዩም ነፍሰ ገዳዩን ባገኘው ጊዜ ይገድለዋል።
“‘ይሁን እንጂ ሰውየው ግለሰቡን የገፈተረው በጥላቻ ተነሳስቶ ሳይሆን ሳያስበው ከሆነ ወይም ዕቃ የወረወረበት ተንኮል አስቦ ካልሆነ
አሊያም ግለሰቡ ሳያየው ድንጋይ ቢጥልበትና ቢሞት ሆኖም ሰውየው ከግለሰቡ ጋር ጠላትነት ባይኖረውና ይህን ያደረገው እሱን ለመጉዳት አስቦ ባይሆን
ማኅበረሰቡ እነዚህን ደንቦች መሠረት በማድረግ በገዳዩና በደም ተበቃዩ መካከል ፍርድ ይስጥ።
ማኅበረሰቡም ነፍሰ ገዳዩን ከደም ተበቃዩ እጅ ታድጎ ሸሽቶበት ወደነበረው የመማጸኛ ከተማ ይመልሰው፤ እሱም በቅዱስ ዘይት የተቀባው ሊቀ ካህናት እስኪሞት ድረስ በዚያ ይቆይ።
“‘ይሁንና ገዳዩ ሸሽቶ ከገባበት የመማጸኛ ከተማ ወሰን ቢወጣና
ደም ተበቃዩም ገዳዩን ከመማጸኛ ከተማው ወሰን ውጭ አግኝቶ ቢገድለው በደም ዕዳ አይጠየቅም።
ምክንያቱም ሊቀ ካህናቱ እስኪሞት ድረስ በመማጸኛ ከተማው ውስጥ መቆየት ይገባዋል። ሊቀ ካህናቱ ከሞተ በኋላ ግን ገዳዩ ወደ ርስቱ መመለስ ይችላል።
እነዚህም በምትኖሩበት በየትኛውም ቦታ በትውልዶቻችሁ ሁሉ ፍርድ ለመስጠት እንደሚያገለግል ደንብ ይሁኗችሁ።
“‘ሰው የገደለ ማንኛውም ሰው ምሥክሮች ከመሠከሩበት እንደ ነፍሰ ገዳይ ተቆጥሮ ይገደል፤ ይሁን እንጂ ማንም ሰው አንድ ግለሰብ በሚሰጠው ምሥክርነት ብቻ በሞት መቀጣት የለበትም።
ሞት ለሚገባው ነፍሰ ገዳይ ሕይወት ቤዛ አትቀበሉ፤ ምክንያቱም ያለምንም ጥርጥር መገደል አለበት።
እንዲሁም ሸሽቶ ወደ መማጸኛ ከተማው ለገባ ሰው ሊቀ ካህናቱ ከመሞቱ በፊት ወደ ምድሩ ተመልሶ እንዲኖር ለማድረግ ቤዛ አትቀበሉ።
“‘ደም ምድሪቱን ስለሚበክል ያላችሁባትን ምድር አትበክሉ፤ ደም ባፈሰሰው ሰው ደም ካልሆነ በስተቀር በምድሪቱ ላይ ለፈሰሰው ደም ስርየት ሊኖር አይችልም።
የምትኖሩባትን፣ እኔም የምኖርባትን ምድር አታርክሱ፤ እኔ ይሖዋ በእስራኤል ሕዝብ መካከል እኖራለሁና።’”
በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦
“ለእስራኤላውያን ይህን መመሪያ ስጣቸው፦ ‘ወደ ከነአን ምድር ስትገቡ ርስት አድርጋችሁ የምትወርሷት ምድር ይኸውም የከነአን ምድር ከነወሰኖቿ ይህች ናት።
“‘በስተ ደቡብ ያለው ወሰናችሁ ከጺን ምድረ በዳ ተነስቶ እስከ ኤዶም ጠረፍ ድረስ ይዘልቃል፤ በስተ ምሥራቅ ያለው ደቡባዊ ወሰናችሁ ደግሞ ከጨው ባሕር ዳርቻ ጀምሮ ያለው ይሆናል።
ወሰናችሁ አቅጣጫውን በመቀየር ከአቅራቢም አቀበት በስተ ደቡብ አድርጎ እስከ ጺን ድረስ ይዘልቃል፤ መጨረሻውም ከቃዴስበርኔ በስተ ደቡብ ይሆናል። ከዚያም ወደ ሃጻርአዳር ይሄድና ወደ አጽሞን ይዘልቃል።
ወሰኑ አጽሞን ላይ ሲደርስ አቅጣጫውን ቀይሮ ወደ ግብፅ ደረቅ ወንዝ ይሄዳል፤ መጨረሻውም ባሕሩ ይሆናል።
“‘ምዕራባዊ ወሰናችሁ ደግሞ ታላቁ ባሕርና የባሕሩ ዳርቻ ይሆናል። ይህ ምዕራባዊ ወሰናችሁ ይሆናል።
“‘ሰሜናዊ ወሰናችሁ የሚከተለው ይሆናል፦ ከታላቁ ባሕር አንስቶ እስከ ሆር ተራራ ድረስ ምልክት በማድረግ ወሰናችሁን ከልሉ።
ከሆር ተራራም አንስቶ እስከ ሌቦሃማት ድረስ ወሰኑን ምልክት አድርጉ፤ የወሰኑም መጨረሻ ጼዳድ ይሆናል።
ወሰኑም እስከ ዚፍሮን ድረስ ይዘልቃል፤ መጨረሻውም ሃጻርኤናን ይሆናል። ይህ ሰሜናዊ ወሰናችሁ ይሆናል።
“‘ከዚያም በስተ ምሥራቅ በኩል ወሰናችሁን ከሃጻርኤናን አንስቶ እስከ ሸፋም ድረስ ምልክት አድርጉ።
ወሰኑም ከሸፋም አንስቶ ከአይን በስተ ምሥራቅ እስከሚገኘው እስከ ሪብላ ድረስ ይዘልቃል፤ ከዚያም ቁልቁል ወርዶ የኪኔሬትን ባሕር ምሥራቃዊ ዳርቻ አቋርጦ ያልፋል።
ወሰኑ ወደ ዮርዳኖስ ይወርድና መጨረሻው ጨው ባሕር ይሆናል። እንግዲህ ምድራችሁ በዙሪያዋ ካሉት ወሰኖቿ ጋር ይህች ናት።’”
በመሆኑም ሙሴ እስራኤላውያንን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ “ይሖዋ ለዘጠኙ ነገዶችና ለግማሹ ነገድ እንዲሰጥ ባዘዘው መሠረት ርስት አድርጋችሁ በዕጣ የምትከፋፈሏት ምድር ይህች ናት።
የሮቤላውያን ነገድ በየአባቶቻቸው ቤት፣ የጋዳውያን ነገድ በየአባቶቻቸው ቤት እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ አስቀድመው ርስታቸውን ወስደዋልና።
ሁለቱ ነገድና ግማሹ ነገድ በኢያሪኮ አቅራቢያ ከዮርዳኖስ ክልል በስተ ምሥራቅ በፀሐይ መውጫ አቅጣጫ ርስታቸውን አግኝተዋል።”
በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦
“ምድሪቱን ለእናንተ ርስት አድርገው የሚያከፋፍሏችሁ ካህኑ አልዓዛርና የነዌ ልጅ ኢያሱ ናቸው።
ምድሪቱን ርስት አድርጋችሁ ለማከፋፈል ከእያንዳንዱ ነገድ አንድ አንድ አለቃ ትወስዳላችሁ።
የሰዎቹም ስም የሚከተለው ነው፦ ከይሁዳ ነገድ የየፎኒ ልጅ ካሌብ፣
ከስምዖን ልጆች ነገድ የአሚሁድ ልጅ ሸሙኤል፣
ከቢንያም ነገድ የኪስሎን ልጅ ኤሊዳድ፣
ከዳን ልጆች ነገድ አንድ አለቃ ይኸውም የዮግሊ ልጅ ቡቂ፣
ከዮሴፍ ልጆች መካከል ከምናሴ ልጆች ነገድ አንድ አለቃ ይኸውም የኤፎድ ልጅ ሃኒኤል፣
ከኤፍሬም ልጆች ነገድ አንድ አለቃ ይኸውም የሺፍጣን ልጅ ቀሙኤል፣
ከዛብሎን ልጆች ነገድ አንድ አለቃ ይኸውም የፓርናክ ልጅ ኤሊጻፋን፣
ከይሳኮር ልጆች ነገድ አንድ አለቃ ይኸውም የአዛን ልጅ ፓልጢኤል፣
ከአሴር ልጆች ነገድ አንድ አለቃ ይኸውም የሸሎሚ ልጅ አሂሑድ፣
ከንፍታሌም ልጆች ነገድ አንድ አለቃ ይኸውም የአሚሁድ ልጅ ፐዳሄል።”
ይሖዋ በከነአን ምድር ለእስራኤላውያን መሬቱን እንዲያከፋፍሉ ያዘዛቸው እነዚህ ናቸው።
በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦
“እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘አንድ ወንድ ወይም አንዲት ሴት ለይሖዋ ናዝራዊ ሆነው ለመኖር ልዩ ስእለት ቢሳሉ
ስእለት የተሳለው ሰው ከወይን ጠጅና ከሚያሰክር ሌላ መጠጥ መራቅ ይኖርበታል። የወይን ጠጅ ኮምጣጤ ወይም የማንኛውም ዓይነት የሚያሰክር መጠጥ ኮምጣጤ አይጠጣ። ከወይን ፍሬ የተዘጋጀን ማንኛውንም መጠጥ አይጠጣ፤ የወይን ፍሬም ሆነ ዘቢብ አይብላ።
ናዝራዊ ሆኖ በሚቆይበት ጊዜ ሁሉ ከወይን ተክል የተዘጋጀን ማንኛውንም ነገር፣ ያልበሰለውን የወይን ፍሬም ሆነ ግልፋፊውን ፈጽሞ መብላት የለበትም።
“‘ናዝራዊ ሆኖ ለመቆየት በተሳለበት ጊዜ ሁሉ ራሱን ምላጭ አይንካው። ለይሖዋ የተለየበት ጊዜ እስኪያበቃ ድረስ የራስ ፀጉሩን በማሳደግ ቅዱስ ሆኖ መገኘት ይኖርበታል።
ራሱን ለይሖዋ በለየበት ጊዜ ሁሉ ወደ ሞተ ሰው አይቅረብ።
ለአምላኩ ናዝራዊ መሆኑን የሚያሳየው ምልክት በራሱ ላይ ስላለ አባቱ ወይም እናቱ ወይም ወንድሙ ወይም እህቱ ቢሞቱ እንኳ በእነሱ ራሱን አያርክስ።
“‘ናዝራዊ ሆኖ በሚቆይበት ጊዜ ሁሉ ለይሖዋ ቅዱስ ይሆናል።
ይሁንና አንድ ሰው ድንገት አጠገቡ ቢሞትና ለአምላክ የተለየ መሆኑን የሚያሳየውን ፀጉሩን ቢያረክስ መንጻቱን በሚያረጋግጥበት ቀን ራሱን ይላጭ። በሰባተኛውም ቀን ፀጉሩን ይላጨው።
በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶችን ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶችን በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ወደሚገኘው ካህን ያምጣ።
ካህኑም አንዱን የኃጢአት መባ ሌላኛውን ደግሞ የሚቃጠል መባ አድርጎ በማዘጋጀት ከሞተ ሰው ጋር በተያያዘ ስለሠራው ኃጢአት ያስተሰርይለታል። ከዚያም በዚያ ቀን ራሱን ይቀድስ።
ናዝራዊ ሆኖ ለሚቆይበት ጊዜ እንደገና ራሱን ለይሖዋ ይለይ፤ አንድ ዓመት ገደማ የሆነው የበግ ጠቦት የበደል መባ አድርጎ ያምጣ። ሆኖም ናዝራዊነቱን ስላረከሰ የቀድሞዎቹ ጊዜያት አይታሰቡለትም።
“‘እንግዲህ ናዝራዊን በተመለከተ ሕጉ ይህ ነው፦ ናዝራዊ ሆኖ የሚቆይበትን ጊዜ ሲያጠናቅቅ ወደ መገናኛ ድንኳኑ መግቢያ እንዲመጣ ይደረግ።