text stringlengths 4 267 |
|---|
በዚያም የሚከተሉትን ለይሖዋ መባ አድርጎ ያቅርብ፦ ለሚቃጠል መባ አንድ ዓመት ገደማ የሆነውን እንከን የሌለበት አንድ የበግ ጠቦት፣ ለኃጢአት መባ አንድ ዓመት ገደማ የሆናትን እንከን የሌለባት አንዲት ጠቦት፣ ለኅብረት መሥዋዕት እንከን የሌለበትን አንድ አውራ በግ፣ |
በዘይት ከተለወሰ የላመ ዱቄት የተዘጋጁ እርሾ ያልገባባቸው አንድ ቅርጫት የቀለበት ቅርጽ ያላቸው ዳቦዎችና ዘይት የተቀቡ ስስ ቂጣዎች እንዲሁም የእህል መባዎቻቸውንና የመጠጥ መባዎቻቸውን። |
ካህኑም እነዚህን በይሖዋ ፊት ያቀርባቸዋል፤ የሰውየውን የኃጢአት መባና የሚቃጠል መባም ያቀርባል። |
አውራውንም በግ በቅርጫቱ ውስጥ ካሉት ቂጣዎች ጋር የኅብረት መሥዋዕት አድርጎ ለይሖዋ ያቀርበዋል፤ ካህኑም የእህል መባውንና የመጠጥ መባውን ያቀርበዋል። |
“‘ከዚያም ናዝራዊው ያልተቆረጠውን ፀጉሩን በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ ይላጭ፤ ናዝራዊ ሆኖ በቆየበት ጊዜ ያደገውን የራሱን ፀጉር ወስዶ ከኅብረት መሥዋዕቱ ሥር ባለው እሳት ውስጥ ይጨምረው። |
ናዝራዊው የናዝራዊነት ምልክቱን ከተላጨ በኋላ ካህኑ የአውራውን በግ አንድ የተቀቀለ የፊት እግር፣ ከቅርጫቱም ውስጥ እርሾ ያልገባበት የቀለበት ቅርጽ ያለው አንድ ዳቦ እንዲሁም አንድ ስስ ቂጣ ወስዶ በናዝራዊው መዳፍ ላይ ያድርጋቸው። |
ካህኑም እነዚህን የሚወዘወዝ መባ አድርጎ በይሖዋ ፊት ወዲያና ወዲህ ይወዝውዛቸው። ይህም ከሚወዘወዘው መባ ፍርምባና መዋጮ ሆኖ ከተሰጠው እግር ጋር ለካህኑ የተቀደሰ ይሆናል። ከዚህ በኋላ ናዝራዊው የወይን ጠጅ መጠጣት ይችላል። |
“‘ስእለት የሚሳልን ናዝራዊ በተመለከተ ሕጉ ይህ ነው፦ ናዝራዊው ስእለት ከተሳለና በናዝራዊነት ከሚጠበቅበት በተጨማሪ ለይሖዋ መባ ለማቅረብ አቅሙ የሚፈቅድለት ከሆነ ለናዝራዊነቱ ሕግ ካለው አክብሮት የተነሳ ስእለቱን መፈጸም ይገባዋል።’” |
ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ |
“አሮንንና ወንዶች ልጆቹን እንዲህ በላቸው፦ ‘የእስራኤልን ሕዝብ የምትባርኩት በዚህ መንገድ ነው። እንዲህ በሏቸው፦ |
“ይሖዋ ይባርክህ፤ ደግሞም ይጠብቅህ። |
ይሖዋ ፊቱን ያብራልህ፤ ሞገሱንም ያሳይህ። |
ይሖዋ ፊቱን ወደ አንተ ይመልስ፤ ሰላምም ይስጥህ።”’ |
እኔም እንድባርካቸው ስሜን በእስራኤል ሕዝብ ላይ ያድርጉ።” |
“‘በሰባተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ቅዱስ ጉባኤ አድርጉ። ምንም ዓይነት ከባድ ሥራ መሥራት የለባችሁም። ይህም መለከት የምትነፉበት ቀን ነው። |
እናንተም አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግ እንዲሁም እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ መዓዛ ያለው የሚቃጠል መባ አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ፤ ሁሉም እንከን የሌለባቸው መሆን ይኖርባቸዋል፤ |
ከእነዚህም ጋር ለወይፈኑ ሦስት አሥረኛ የኢፍ መስፈሪያ፣ ለአውራው በግ ደግሞ ሁለት አሥረኛ መስፈሪያ በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት የእህል መባ አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ፤ |
ለሰባቱ ተባዕት የበግ ጠቦቶች ለእያንዳንዳቸው አንድ አሥረኛ መስፈሪያ በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት ታቀርባላችሁ፤ |
እንዲሁም ለእናንተ ማስተሰረያ እንዲሆን አንድ ተባዕት የፍየል ጠቦት የኃጢአት መባ አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ። |
ይህም በተለመደው አሠራር መሠረት ከሚቀርቡት ከወርሃዊው የሚቃጠል መባና አብሮት ከሚቀርበው የእህል መባ፣ ከዘወትሩ የሚቃጠል መባና አብሮት ከሚቀርበው የእህል መባ እንዲሁም ከመጠጥ መባዎቻቸው በተጨማሪ ደስ የሚያሰኝ መዓዛ ያለው ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ ነው። |
“‘በዚሁ በሰባተኛው ወር በአሥረኛው ቀን ቅዱስ ጉባኤ አድርጉ፤ ራሳችሁን አጎሳቁሉ። ምንም ዓይነት ሥራ አትሥሩ። |
አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግ እንዲሁም እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ደስ የሚያሰኝ መዓዛ ያለው ለይሖዋ የሚቃጠል መባ አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ፤ ሁሉም እንከን የሌለባቸው መሆን ይኖርባቸዋል። |
ከእነዚህም ጋር ለወይፈኑ ሦስት አሥረኛ መስፈሪያ፣ ለአውራው በግ ደግሞ ሁለት አሥረኛ መስፈሪያ በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት የእህል መባ አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ፤ |
እንዲሁም ለሰባቱ ተባዕት የበግ ጠቦቶች ለእያንዳንዳቸው አንድ አሥረኛ መስፈሪያ በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት ታቀርባላችሁ፤ |
ለማስተሰረያ ከሚሆነው የኃጢአት መባ፣ ከዘወትሩ የሚቃጠል መባና አብሮት ከሚቀርበው የእህል መባ እንዲሁም ከመጠጥ መባዎቻቸው በተጨማሪ አንድ የፍየል ጠቦት የኃጢአት መባ አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ። |
“‘በሰባተኛው ወር በ15ኛው ቀን ቅዱስ ጉባኤ አድርጉ። ምንም ዓይነት ከባድ ሥራ አትሥሩ፤ ለሰባት ቀንም ለይሖዋ በዓል አክብሩ። |
እንዲሁም 13 ወይፈኖች፣ 2 አውራ በጎችና እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው 14 ተባዕት የበግ ጠቦቶች የሚቃጠል መባ ይኸውም ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ መዓዛ ያለው በእሳት የሚቀርብ መባ አድርጋችሁ አቅርቡ፤ ሁሉም እንከን የሌለባቸው መሆን ይኖርባቸዋል። |
ከእነዚህም ጋር ለ13ቱ ወይፈኖች ለእያንዳንዳቸው ሦስት አሥረኛ መስፈሪያ፣ ለ2ቱ አውራ በጎች ደግሞ ለእያንዳንዳቸው ሁለት አሥረኛ መስፈሪያ በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት የእህል መባ አድርጋችሁ አቅርቡ፤ |
እንዲሁም ለ14ቱ ተባዕት የበግ ጠቦቶች ለእያንዳንዳቸው አንድ አሥረኛ መስፈሪያ በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት አቅርቡ፤ |
ከዘወትሩ የሚቃጠል መባ እንዲሁም አብሮት ከሚቀርበው የእህል መባና የመጠጥ መባ በተጨማሪ አንድ የፍየል ጠቦት የኃጢአት መባ አድርጋችሁ አቅርቡ። |
“‘በሁለተኛው ቀን 12 ወይፈኖች፣ 2 አውራ በጎች እንዲሁም እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው 14 ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ፤ ሁሉም እንከን የሌለባቸው መሆን ይኖርባቸዋል፤ |
ለወይፈኖቹ፣ ለአውራ በጎቹና ለተባዕት የበግ ጠቦቶቹ በተለመደው አሠራር መሠረት በቁጥራቸው ልክ የእህል መባቸውንና የመጠጥ መባዎቻቸውን አቅርቡ፤ |
ከዘወትሩ የሚቃጠል መባና አብሮት ከሚቀርበው የእህል መባ እንዲሁም ከመጠጥ መባዎቻቸው በተጨማሪ አንድ የፍየል ጠቦት የኃጢአት መባ አድርጋችሁ አቅርቡ። |
“‘በሦስተኛው ቀን 11 ወይፈኖች፣ 2 አውራ በጎች እንዲሁም እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው 14 ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ፤ ሁሉም እንከን የሌለባቸው መሆን ይኖርባቸዋል፤ |
ለወይፈኖቹ፣ ለአውራ በጎቹና ለተባዕት የበግ ጠቦቶቹ በተለመደው አሠራር መሠረት በቁጥራቸው ልክ የእህል መባቸውንና የመጠጥ መባዎቻቸውን አቅርቡ፤ |
ከዘወትሩ የሚቃጠል መባ እንዲሁም አብሮት ከሚቀርበው የእህል መባና የመጠጥ መባ በተጨማሪ አንድ ፍየል የኃጢአት መባ አድርጋችሁ አቅርቡ። |
“‘በአራተኛው ቀን 10 ወይፈኖች፣ 2 አውራ በጎች እንዲሁም እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው 14 ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ፤ ሁሉም እንከን የሌለባቸው መሆን ይኖርባቸዋል፤ |
ለወይፈኖቹ፣ ለአውራ በጎቹና ለተባዕት የበግ ጠቦቶቹ በተለመደው አሠራር መሠረት በቁጥራቸው ልክ የእህል መባቸውንና የመጠጥ መባዎቻቸውን አቅርቡ፤ |
ከዘወትሩ የሚቃጠል መባ እንዲሁም አብሮት ከሚቀርበው የእህል መባና የመጠጥ መባ በተጨማሪ አንድ የፍየል ጠቦት የኃጢአት መባ አድርጋችሁ አቅርቡ። |
“‘በአምስተኛው ቀን 9 ወይፈኖች፣ 2 አውራ በጎች እንዲሁም እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው 14 ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ፤ ሁሉም እንከን የሌለባቸው መሆን ይኖርባቸዋል፤ |
ለወይፈኖቹ፣ ለአውራ በጎቹና ለተባዕት የበግ ጠቦቶቹ በተለመደው አሠራር መሠረት በቁጥራቸው ልክ የእህል መባቸውንና የመጠጥ መባዎቻቸውን አቅርቡ፤ |
ከዘወትሩ የሚቃጠል መባ እንዲሁም አብሮት ከሚቀርበው የእህል መባና የመጠጥ መባ በተጨማሪ አንድ ፍየል የኃጢአት መባ አድርጋችሁ አቅርቡ። |
“‘በስድስተኛውም ቀን 8 ወይፈኖች፣ 2 አውራ በጎች እንዲሁም እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው 14 ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ፤ ሁሉም እንከን የሌለባቸው መሆን ይኖርባቸዋል፤ |
ለወይፈኖቹ፣ ለአውራ በጎቹና ለተባዕት የበግ ጠቦቶቹ በተለመደው አሠራር መሠረት በቁጥራቸው ልክ የእህል መባቸውንና የመጠጥ መባዎቻቸውን አቅርቡ፤ |
ከዘወትሩ የሚቃጠል መባ እንዲሁም አብረውት ከሚቀርቡት የእህል መባና የመጠጥ መባዎች በተጨማሪ አንድ ፍየል የኃጢአት መባ አድርጋችሁ አቅርቡ። |
“‘በሰባተኛው ቀን 7 ወይፈኖች፣ 2 አውራ በጎች እንዲሁም እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው 14 ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ፤ ሁሉም እንከን የሌለባቸው መሆን ይኖርባቸዋል፤ |
ለወይፈኖቹ፣ ለአውራ በጎቹና ለተባዕት የበግ ጠቦቶቹ በተለመደው አሠራር መሠረት በቁጥራቸው ልክ የእህል መባቸውንና የመጠጥ መባዎቻቸውን አቅርቡ፤ |
ከዘወትሩ የሚቃጠል መባ እንዲሁም አብሮት ከሚቀርበው የእህል መባና የመጠጥ መባ በተጨማሪ አንድ ፍየል የኃጢአት መባ አድርጋችሁ አቅርቡ። |
“‘በስምንተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ። ምንም ዓይነት ከባድ ሥራ መሥራት የለባችሁም። |
አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግ እንዲሁም እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች የሚቃጠል መባ ይኸውም ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ መዓዛ ያለው በእሳት የሚቀርብ መባ አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ፤ ሁሉም እንከን የሌለባቸው መሆን ይኖርባቸዋል፤ |
ለወይፈኑ፣ ለአውራው በግና ለተባዕት የበግ ጠቦቶቹ በተለመደው አሠራር መሠረት በቁጥራቸው ልክ የእህል መባቸውንና የመጠጥ መባዎቻቸውን አቅርቡ፤ |
ከዘወትሩ የሚቃጠል መባ እንዲሁም አብሮት ከሚቀርበው የእህል መባና የመጠጥ መባ በተጨማሪ አንድ ፍየል የኃጢአት መባ አድርጋችሁ አቅርቡ። |
“‘እነዚህም የሚቃጠሉ መባዎች፣ የእህል መባዎች፣ የመጠጥ መባዎችና የኅብረት መሥዋዕቶች አድርጋችሁ ከምታቀርቧቸው የስእለት መባዎችና የፈቃደኝነት መባዎች በተጨማሪ በየወቅቱ በምታከብሯቸው በዓላት ላይ ለይሖዋ የምታቀርቧቸው ናቸው።’” |
ሙሴም ይሖዋ ያዘዘውን ነገር በሙሉ ለእስራኤላውያን ነገራቸው። |
ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ |
“ለአሮን ‘መብራቶቹን በምታበራበት ጊዜ ሰባቱ መብራቶች በመቅረዙ ፊት ለፊት ላለው አካባቢ ብርሃን መስጠት ይኖርባቸዋል’ ብለህ ንገረው።” |
አሮንም እንዲሁ አደረገ፤ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት በመቅረዙ ፊት ለፊት ያለው አካባቢ ብርሃን እንዲያገኝ የመቅረዙን መብራቶች ለኮሳቸው። |
የመቅረዙ አሠራር ይህ ነበር፦ አንድ ወጥ ከሆነ ወርቅ ተጠፍጥፎ የተሠራ ነበር፤ ግንዱም ሆነ የፈኩት አበቦቹ ወጥ ከሆነ ወርቅ ተጠፍጥፈው የተሠሩ ነበሩ። መቅረዙ የተሠራው ይሖዋ ለሙሴ ባሳየው ራእይ መሠረት ነበር። |
ይሖዋ ሙሴን ዳግመኛ እንዲህ አለው፦ |
“ሌዋውያኑን ከእስራኤላውያን መካከል ወስደህ አንጻቸው። |
እነሱንም የምታነጻቸው በሚከተለው መንገድ ነው፦ ከኃጢአት የሚያነጻ ውኃ እርጫቸው፤ እነሱም ሰውነታቸውን በሙሉ በምላጭ ይላጩ፤ እንዲሁም ልብሳቸውን ይጠቡ፤ ራሳቸውንም ያንጹ። |
ከዚያም አንድ ወይፈንና አብሮት የሚቀርበውን በዘይት ከተለወሰ የላመ ዱቄት የተዘጋጀ የእህል መባ ይወስዳሉ፤ አንተም ለኃጢአት መባ እንዲሆን ሌላ ወይፈን ትወስዳለህ። |
እንዲሁም ሌዋውያኑን በመገናኛ ድንኳኑ ፊት ታቀርባቸዋለህ፤ መላውን የእስራኤል ማኅበረሰብ ትሰበስባለህ። |
ሌዋውያኑን በይሖዋ ፊት በምታቀርባቸው ጊዜ እስራኤላውያን በሌዋውያኑ ላይ እጆቻቸውን ይጫኑ። |
አሮንም ከእስራኤላውያን መካከል ሌዋውያኑን እንደሚወዘወዝ መባ አድርጎ በይሖዋ ፊት ያቅርባቸው፤ እነሱም ለይሖዋ የሚቀርበውን አገልግሎት ያከናውናሉ። |
“ከዚያም ሌዋውያኑ በወይፈኖቹ ራስ ላይ እጆቻቸውን በመጫን ለእነሱ ማስተሰረያ እንዲሆኑ አንደኛውን ወይፈን የኃጢአት መባ ሌላኛውን ደግሞ የሚቃጠል መባ አድርገው ለይሖዋ ያቀርባሉ። |
ሌዋውያኑንም በአሮንና በወንዶች ልጆቹ ፊት እንዲቆሙ ካደረግክ በኋላ እንደሚወዘወዝ መባ አድርገህ ለይሖዋ አቅርባቸው። |
ሌዋውያኑን ከእስራኤላውያን መካከል ለያቸው፤ ሌዋውያኑም የእኔ ይሆናሉ። |
ከዚህ በኋላ ሌዋውያኑ በመገናኛ ድንኳኑ ለማገልገል ይመጣሉ። እነሱን የምታነጻቸውና እንደሚወዘወዝ መባ አድርገህ የምታቀርባቸው በዚህ መንገድ ነው። |
ምክንያቱም እነሱ የተሰጡ ይኸውም ከእስራኤላውያን መካከል ለእኔ የተሰጡ ናቸው። በእስራኤላውያን በኩሮች ሁሉ ምትክ እነሱን ለራሴ እወስዳቸዋለሁ። |
ምክንያቱም ሰውም ሆነ እንስሳ ከእስራኤላውያን መካከል በኩር የሆነ ሁሉ የእኔ ነው። በግብፅ ምድር ያለውን በኩር ሁሉ በመታሁበት ቀን እነሱን ለራሴ ቀድሻቸዋለሁ። |
ሌዋውያኑን በእስራኤላውያን በኩር ሁሉ ምትክ እወስዳቸዋለሁ። |
የእስራኤል ሕዝብ ወደ ቅዱሱ ስፍራ በመቅረቡ የተነሳ በመካከሉ መቅሰፍት እንዳይከሰት በእስራኤላውያን ምትክ በመገናኛ ድንኳኑ ያገለግሉና ለእነሱ ያስተሰርዩ ዘንድ ከእስራኤላውያን መካከል ሌዋውያኑን ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ የተሰጡ አድርጌ እሰጣቸዋለሁ።” |
ሙሴ፣ አሮንና መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ሁሉ ለሌዋውያኑ እንዲሁ አደረጉ። እስራኤላውያንም ይሖዋ ሌዋውያኑን አስመልክቶ ሙሴን ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ። |
በመሆኑም ሌዋውያኑ ራሳቸውን አነጹ፤ ልብሶቻቸውንም አጠቡ፤ በመቀጠልም አሮን እንደሚወዘወዝ መባ አድርጎ በይሖዋ ፊት አቀረባቸው። ከዚያም አሮን እነሱን ለማንጻት ማስተሰረያ አቀረበላቸው። |
ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ሌዋውያኑ በመገናኛ ድንኳኑ በአሮንና በወንዶች ልጆቹ ፊት አገልግሎታቸውን ለመፈጸም ገቡ። ይሖዋ ሌዋውያኑን በተመለከተ ሙሴን ባዘዘው መሠረት እንዲሁ አደረጉላቸው። |
በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ |
“ሌዋውያኑን በተመለከተ የተደረገው ዝግጅት የሚከተለው ነው፦ አንድ ወንድ ዕድሜው 25 ዓመትና ከዚያ በላይ ከሆነ በመገናኛ ድንኳኑ ከሚያገለግለው ቡድን ጋር ይቀላቀላል። |
ዕድሜው 50 ዓመት ከሞላ ግን ከሚያገለግልበት ቡድን ጡረታ ይወጣል፤ ከዚያ በኋላ ማገልገል አይጠበቅበትም። |
ይህ ሰው በመገናኛ ድንኳኑ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ያሉትን ወንድሞቹን ሊያገለግል ይችላል፤ ሆኖም በዚያ ማገልገል የለበትም። ሌዋውያኑንና የተጣለባቸውን ኃላፊነት በተመለከተ ማድረግ ያለብህ ይህን ነው።” |
“እንከን ወይም ማንኛውም ዓይነት ጉድለት ያለበትን በሬ ወይም በግ ለአምላክህ ለይሖዋ አትሠዋ፤ ምክንያቱም ይህ ለአምላክህ ለይሖዋ አስጸያፊ ነው። |
“አምላክህ ይሖዋ ከሚሰጥህ ከተሞች በአንዱ ውስጥ በአምላክህ በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር የሚፈጽምና ቃል ኪዳኑን የሚያፈርስ ወንድ ወይም ሴት ቢገኝ |
እሱም ሄዶ ሌሎች አማልክትን በማምለክ እንዲሁም ለእነሱ ወይም ለፀሐይ አሊያም ለጨረቃ ወይም ደግሞ ለሰማይ ሠራዊት በሙሉ በመስገድ እኔ ያላዘዝኩትን ነገር ቢያደርግ |
አንተም ይህ ነገር ቢነገርህ ወይም ሁኔታውን ብትሰማ ጉዳዩን በጥንቃቄ አጣራ። ይህ አስጸያፊ ነገር በእስራኤል ውስጥ መፈጸሙ እውነት እንደሆነ ቢረጋገጥ |
እንዲህ ያለ መጥፎ ድርጊት የፈጸመውን ያንን ሰው ወይም ያቺን ሴት ወደ ከተማዋ በር አውጣቸው፤ ከዚያም ሰውየው ወይም ሴትየዋ እስኪሞቱ ድረስ በድንጋይ ይወገሩ። |
ሞት የሚገባው ሰው ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች በሚሰጡት ምሥክርነት ይገደል። አንድ ምሥክር በሚሰጠው ቃል ብቻ መገደል የለበትም። |
እሱን ለመግደል መጀመሪያ እጃቸውን የሚያነሱት ምሥክሮቹ መሆን ይኖርባቸዋል፤ ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ እጁን ያንሳበት። ክፉ የሆነውን ከመካከልህ አስወግድ። |
“ከከተሞችህ በአንዱ ውስጥ ለመዳኘት አስቸጋሪ የሆነ ክርክር ቢነሳ ለምሳሌ፣ ጉዳዩ ደም ማፍሰስን የሚመለከትም ይሁን ለሕግ አቤቱታ ማቅረብን ወይም የዓመፅ ድርጊትን አሊያም ሌሎች አለመግባባቶችን የሚመለከት ቢሆን ተነስተህ አምላክህ ይሖዋ ወደሚመርጠው ስፍራ ውጣ። |
ወደ ሌዋውያን ካህናትና በዚያን ጊዜ ዳኛ ሆኖ ወደሚያገለግለው ሰው ሄደህ ጠይቅ፤ እነሱም ውሳኔውን ይነግሩሃል። |
አንተም እነዚህ ሰዎች ይሖዋ በሚመርጠው ስፍራ ሆነው በነገሩህ ውሳኔ መሠረት እርምጃ ውሰድ። የሰጡህንም መመሪያ በሙሉ በጥንቃቄ ፈጽም። |
በሚሰጡህ ሕግና በሚነግሩህ ውሳኔ መሠረት እርምጃ ውሰድ። እነሱ ካሳለፉት ውሳኔ ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ዞር አትበል። |
አምላክህን ይሖዋን የሚያገለግለውን ካህን ወይም ዳኛውን ባለመስማት እብሪተኛ የሚሆን ሰው ካለ ይገደል። ክፉ የሆነውን ከእስራኤል መካከል አስወግድ። |
ሕዝቡም ሁሉ ይህን ሲሰማ ይፈራል፤ ከእንግዲህም የእብሪት ድርጊት አይፈጽምም። |
“አምላክህ ይሖዋ የሚሰጥህን ምድር ገብተህ ከወረስካት በኋላ በዚያ መኖር ስትጀምር ‘በዙሪያዬ እንዳሉት ብሔራት ሁሉ እኔም በላዬ ላይ ንጉሥ ላንግሥ’ ብትል |
አምላክህ ይሖዋ የሚመርጠውን ንጉሥ ታነግሣለህ። የምታነግሠውም ንጉሥ ከወንድሞችህ መካከል መሆን ይኖርበታል። ወንድምህ ያልሆነን ባዕድ ሰው በላይህ ላይ ማንገሥ አይገባህም። |
ይሁን እንጂ ንጉሡ ለራሱ ፈረሶች ማብዛት ወይም የፈረሶቹን ቁጥር ለመጨመር ሲል ሕዝቡ ወደ ግብፅ እንዲመለስ ማድረግ የለበትም፤ ምክንያቱም ይሖዋ ‘በዚህ መንገድ ፈጽሞ ዳግመኛ አንዳትመለሱ’ ብሏችኋል። |
ልቡ ከትክክለኛው መንገድ ዞር እንዳይል ለራሱ ሚስቶች አያብዛ፤ ለራሱም ብርና ወርቅ አያከማች። |
በመንግሥቱ ዙፋን ላይ በሚቀመጥበትም ጊዜ በሌዋውያን ካህናት እጅ ካለው ላይ ወስዶ የዚህን ሕግ ቅጂ ለራሱ በመጽሐፍ ላይ ይጻፍ። |
“አምላኩን ይሖዋን መፍራትን እንዲማር እንዲሁም በዚህ ሕግና በእነዚህ ሥርዓቶች ላይ የሰፈሩትን ቃላት በሙሉ በመፈጸም እንዲጠብቃቸው ይህ መጽሐፍ ከእሱ ጋር ይሁን፤ በሕይወት ዘመኑም ሁሉ ያንብበው። |
ይህን ካደረገ ልቡ በወንድሞቹ ላይ አይታበይም፤ ከትእዛዛቱም ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ዞር አይልም፤ ይህም እሱም ሆነ ልጆቹ በእስራኤል መካከል በመንግሥቱ ላይ ረጅም ዘመን እንዲቆዩ ያስችላቸዋል። |
Subsets and Splits
No community queries yet
The top public SQL queries from the community will appear here once available.