text
stringlengths
4
267
ይህን ካደረጋችሁ ሰማይ ከምድር በላይ እስካለ ድረስ ይሖዋ ለአባቶቻችሁ ለመስጠት በማለላቸው ምድር ላይ የእናንተም ሆነ የልጆቻችሁ ዕድሜ ይረዝማል።
“አምላካችሁን ይሖዋን እንድትወዱ፣ በመንገዶቹ ሁሉ እንድትሄዱና ከእሱ ጋር እንድትጣበቁ የሰጠኋችሁን እነዚህን ሁሉ ትእዛዛት በጥብቅ ብትከተሉና ብትፈጽሟቸው
ይሖዋም እነዚህን ሁሉ ብሔራት ከፊታችሁ ያባርራቸዋል፤ እናንተም ከእናንተ ይልቅ ታላቅ የሆኑትንና ብዙ ሕዝብ ያላቸውን ብሔራት ታስለቅቃላችሁ።
እግራችሁ የረገጠው ቦታ ሁሉ የእናንተ ይሆናል። ወሰናችሁም ከምድረ በዳው አንስቶ እስከ ሊባኖስ እንዲሁም ከወንዙ ይኸውም ከኤፍራጥስ ወንዝ አንስቶ በስተ ምዕራብ እስካለው ባሕር ድረስ ይሆናል።
ማንም ሰው ሊቋቋማችሁ አይችልም። አምላካችሁ ይሖዋም ቃል በገባላችሁ መሠረት በምትረግጡት ምድር ሁሉ ላይ ሽብርና ፍርሃት ይለቃል።
“እንግዲህ ዛሬ ይህን በረከትና እርግማን በፊታችሁ አስቀምጫለሁ፦
እኔ ዛሬ የማዛችሁን የአምላካችሁን የይሖዋን ትእዛዛት ከፈጸማችሁ በረከቱን ታገኛላችሁ፤
የአምላካችሁን የይሖዋን ትእዛዛት ካልፈጸማችሁና እኔ ዛሬ እንድትከተሉት ከማዛችሁ መንገድ ዞር በማለት የማታውቋቸውን አማልክት ከተከተላችሁ ግን እርግማኑ ይደርስባችኋል።
“አምላካችሁ ይሖዋ ርስት አድርጋችሁ ወደምትወርሷት ምድር በሚያስገባችሁ ጊዜ በረከቱን በገሪዛን ተራራ ላይ እርግማኑን ደግሞ በኤባል ተራራ ላይ ታውጃላችሁ።
እነዚህ ተራሮች የሚገኙት ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ፣ በአረባ በሚኖሩት በከነአናውያን ምድር ከጊልጋል ትይዩ በሞሬ ትላልቅ ዛፎች አጠገብ አይደለም?
አሁን አምላካችሁ ይሖዋ የሚሰጣችሁን ምድር ገብታችሁ ለመውረስ ዮርዳኖስን ልትሻገሩ ነው። እንግዲህ ምድሪቱን ወርሳችሁ በእሷ ላይ ስትኖሩ
ዛሬ በፊታችሁ ያስቀመጥኳቸውን ሥርዓቶችና ድንጋጌዎች በሙሉ በጥንቃቄ ፈጽሙ።
“አምላክህ ይሖዋ ርስት አድርጎ የሚሰጥህን ምድር ገብተህ ስትወርስና በዚያ መኖር ስትጀምር
አምላክህ ይሖዋ ከሚሰጥህ ምድር ከምትሰበስበው ይኸውም ምድሪቱ ከምታፈራው ፍሬ ሁሉ በኩር የሆነውን ወስደህ በቅርጫት ውስጥ በማድረግ አምላክህ ይሖዋ ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን ወደሚመርጠው ስፍራ ይዘህ ሂድ።
በወቅቱ ወደሚያገለግለው ካህን ሄደህ ‘ይሖዋ ለእኛ ለመስጠት ለአባቶቻችን ወደማለላቸው ምድር መግባቴን ዛሬ ለአምላክህ ለይሖዋ አሳውቃለሁ’ በለው።
“ከዚያም ካህኑ ቅርጫቱን ከእጅህ ላይ ወስዶ በአምላክህ በይሖዋ መሠዊያ ፊት ያስቀምጠዋል።
አንተም በአምላክህ በይሖዋ ፊት እንዲህ ብለህ ተናገር፦ ‘አባቴ ዘላን አራማዊ ነበር፤ እሱም ወደ ግብፅ ወርዶ በቁጥር አነስተኛ ከሆነው ቤተሰቡ ጋር የባዕድ አገር ሰው ሆኖ መኖር ጀመረ። ሆኖም በዚያ ሲኖር ኃያልና ቁጥሩ የበዛ ታላቅ ብሔር ሆነ።
ግብፃውያንም ክፉኛ ያንገላቱንና ይጨቁኑን እንዲሁም በላያችን ላይ ከባድ የባርነት ቀንበር ይጭኑብን ነበር።
እኛም ወደ አባቶቻችን አምላክ ወደ ይሖዋ ጮኽን፤ ይሖዋም ጩኸታችንን ሰማ፤ ጉስቁልናችንን፣ መከራችንንና የደረሰብንን ጭቆናም ተመለከተ።
በመጨረሻም ይሖዋ በኃያል እጅና በተዘረጋ ክንድ፣ አስፈሪ ነገሮችን በማድረግ እንዲሁም ድንቅ ምልክቶችን በማሳየትና ተአምራትን በመፈጸም ከግብፅ አወጣን።
ከዚያም ወደዚህ ስፍራ አምጥቶ ይህችን ምድር ይኸውም ወተትና ማር የምታፈሰውን ምድር ሰጠን።
ይኸው አሁን ይሖዋ የሰጠኝ ምድር ካፈራችው ፍሬ በኩር የሆነውን አምጥቻለሁ።’ “ይህን በአምላክህ በይሖዋ ፊት አስቀምጠው፤ አንተም በአምላክህ በይሖዋ ፊት ስገድ።
ከዚያም አንተ፣ ሌዋዊውና በመካከልህ የሚኖረው የባዕድ አገር ሰው አምላክህ ይሖዋ ለአንተና ለቤተሰብህ በሰጠው መልካም ነገር ሁሉ ትደሰታላችሁ።
“የአሥራት ዓመት በሆነው በሦስተኛው ዓመት የምርትህን አንድ አሥረኛ አሥራት እንዲሆን ለይተህ ካስቀመጥክ በኋላ ለሌዋዊው፣ ለባዕድ አገሩ ሰው፣ አባት ለሌለው ልጅና ለመበለቲቱ ትሰጣለህ፤ እነሱም በከተሞችህ ውስጥ እስኪጠግቡ ድረስ ይበሉታል።
ከዚያም በአምላክህ በይሖዋ ፊት እንዲህ ትላለህ፦ ‘በሰጠኸኝ ትእዛዝ መሠረት ቅዱስ የሆነውን ነገር ከቤት አውጥቼ ለሌዋዊው፣ ለባዕድ አገሩ ሰው፣ አባት ለሌለው ልጅና ለመበለቲቱ ሰጥቻለሁ። ትእዛዛትህን አልጣስኩም ወይም ችላ አላልኩም።
ሐዘን ላይ በተቀመጥኩበት ጊዜ ከእሱ አልበላሁም፤ ወይም ረክሼ ባለሁበት ጊዜ ከእሱ ላይ ምንም ነገር አላነሳሁም፤ አሊያም ለሞተ ሰው ከእሱ ላይ ምንም ነገር አልሰጠሁም። የአምላኬን የይሖዋን ቃል ታዝዣለሁ፤ ያዘዝከኝንም ሁሉ ፈጽሜአለሁ።
እንግዲህ አሁን ከቅዱስ ማደሪያህ ከሰማያት ሆነህ ተመልከት፤ ሕዝብህን እስራኤልንና ለአባቶቻችን በማልክላቸው መሠረት የሰጠኸንን ምድር ይኸውም ወተትና ማር የምታፈሰውን ምድር ባርክ።’
“አምላክህ ይሖዋ እነዚህን ሥርዓቶችና ድንጋጌዎች እንድትጠብቅ ዛሬ ያዝሃል። አንተም በሙሉ ልብህና በሙሉ ነፍስህ ፈጽማቸው፤ ጠብቃቸውም።
ይሖዋ በመንገዶቹ ከሄድክ እንዲሁም ሥርዓቶቹን፣ ትእዛዛቱንና ድንጋጌዎቹን ከጠበቅክና ቃሉን ከሰማህ አምላክህ እንደሚሆን ዛሬ ነግሮሃል።
አንተም ይሖዋ ቃል በገባልህ መሠረት ሕዝቡ ማለትም ልዩ ንብረቱ እንደምትሆንና ትእዛዛቱን በሙሉ እንደምትጠብቅ የተናገርከውን ቃል በዛሬው ዕለት ሰምቷል፤
አንተ ለአምላክህ ለይሖዋ ቅዱስ ሕዝብ ሆነህ ስትገኝ እሱ ደግሞ በገባው ቃል መሠረት ውዳሴ፣ ዝናና ክብር በማጎናጸፍ፣ ከፈጠራቸው ሌሎች ብሔራት ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያደርግሃል።”
ሙሴ በዮርዳኖስ ክልል በሚገኘው ምድረ በዳ ይኸውም በፋራን፣ በጦፌል፣ በላባ፣ በሃጼሮት እና በዲዛሃብ መካከል ከሚገኘው ከሱፈ ፊት ለፊት ባለው በረሃማ ሜዳ ላይ ለነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ የተናገረው ቃል ይህ ነው።
ወደ ሴይር ተራራ በሚወስደው መንገድ በኩል ከኮሬብ እስከ ቃዴስበርኔ የ11 ቀን መንገድ ነው።
በ40ኛው ዓመት፣ በ11ኛው ወር፣ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ሙሴ ለእስራኤላውያን እንዲነግራቸው ይሖዋ ባዘዘው መሠረት ነገራቸው።
ይህን ያደረገው በሃሽቦን ይኖር የነበረውን የአሞራውያንን ንጉሥ ሲሖንን ድል ካደረገና በአስታሮት ይኖር የነበረውን የባሳንን ንጉሥ ኦግን ኤድራይ ላይ ካሸነፈ በኋላ ነው።
በዮርዳኖስ ክልል፣ በሞዓብ ምድር ሙሴ ይህን ሕግ እንዲህ በማለት ያብራራ ጀመር፦
“ይሖዋ አምላካችን በኮሬብ እንዲህ አለን፦ ‘በዚህ ተራራማ አካባቢ ለረጅም ጊዜ ቆይታችኋል።
ተነስታችሁ ወደ አሞራውያን ተራራማ አካባቢ እንዲሁም በአረባ፣ በተራራማው አካባቢ፣ በሸፌላ፣ በኔጌብ እና በባሕሩ ዳርቻ ወደሚገኙት ጎረቤቶቻቸው ሁሉ ብሎም ወደ ከነአናውያን ምድርና ወደ ሊባኖስ በመጓዝ እስከ ታላቁ ወንዝ ማለትም እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ሂዱ።
እነሆ በፊታችሁ ይህችን ምድር አስቀምጫለሁ። ይሖዋ ለአባቶቻችሁ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ እንዲሁም ከእነሱ በኋላ ለሚመጡት ዘሮቻቸው ሊሰጣቸው የማለላቸውን ምድር ገብታችሁ ውረሱ።’
“እኔም በዚያን ጊዜ እንዲህ አልኳችሁ፦ ‘እኔ ብቻዬን እናንተን ልሸከማችሁ አልችልም።
ይሖዋ አምላካችሁ ቁጥራችሁን አብዝቶታል፤ ይኸው ዛሬ ከብዛታችሁ የተነሳ በሰማያት ላይ እንዳሉ ከዋክብት ሆናችኋል።
የአባቶቻችሁ አምላክ ይሖዋ ሺህ ጊዜ ያብዛችሁ፤ ደግሞም በገባላችሁ ቃል መሠረት ይባርካችሁ።
ይሁንና እኔ ብቻዬን የእናንተን ሸክምና ጫና እንዲሁም ጠብ እንዴት መሸከም እችላለሁ?
ከየነገዶቻችሁ ጥበበኛና አስተዋይ የሆኑ እንዲሁም ተሞክሮ ያካበቱ ወንዶችን ምረጡ፤ እኔም በእናንተ ላይ መሪ አድርጌ እሾማቸዋለሁ።’
እናንተም ‘አድርጉ ያልከን ነገር መልካም ነው’ በማለት መለሳችሁልኝ።
እኔም ጥበበኛ የሆኑትንና ተሞክሮ ያካበቱትን የየነገዳችሁን መሪዎች ወስጄ የሺህ አለቆች፣ የመቶ አለቆች፣ የሃምሳ አለቆችና የአሥር አለቆች እንዲሁም የየነገዶቻችሁ ሹማምንት አድርጌ በእናንተ ላይ ሾምኳቸው።
“በዚያን ጊዜ ለዳኞቻችሁ ይህን መመሪያ ሰጠኋቸው፦ ‘በወንድሞቻችሁ መካከል የተፈጠረን አንድ ጉዳይ በምትሰሙበት ጊዜ በሰውየውና በወንድሙ ወይም በባዕድ አገሩ ሰው መካከል በጽድቅ ፍረዱ።
በምትፈርዱበት ጊዜ አታዳሉ። ትንሹንም ሆነ ትልቁን እኩል ስሙ። ፍርድ የአምላክ ስለሆነ ሰውን አትፍሩ፤ አንድ ጉዳይ ከከበዳችሁ ወደ እኔ አምጡት፤ እኔም እሰማዋለሁ።’
በዚያን ጊዜ ማድረግ ስላለባችሁ ነገር ሁሉ መመሪያ ሰጠኋችሁ።
“ከዚያም ይሖዋ አምላካችን ባዘዘን መሠረት ከኮሬብ በመነሳት ያን ያያችሁትን ጭልጥ ያለና የሚያስፈራ ምድረ በዳ አቋርጠን ወደ አሞራውያን ተራራማ አካባቢዎች በሚወስደው መንገድ ተጓዝን፤ በመጨረሻም ቃዴስበርኔ ደረስን።
እኔም እንዲህ አልኳችሁ፦ ‘አምላካችን ይሖዋ ወደሚሰጠን ወደ አሞራውያን ተራራማ አካባቢዎች ደርሳችኋል።
ይኸው አምላካችሁ ይሖዋ ምድሪቱን ለእናንተ ሰጥቷችኋል። የአባቶቻችሁ አምላክ ይሖዋ በነገራችሁ መሠረት ተነሱና ውረሷት። አትፍሩ ወይም አትሸበሩ።’
“ሆኖም እናንተ ሁላችሁም ወደ እኔ መጥታችሁ እንዲህ አላችሁኝ፦ ‘ምድሪቱን እንዲሰልሉልን እንዲሁም በየትኛው መንገድ መሄድ እንደሚኖርብንና ምን ዓይነት ከተሞች እንደሚያጋጥሙን አይተው እንዲነግሩን ሰዎችን አስቀድመን እንላክ።’
ይህም ሐሳብ መልካም መስሎ ታየኝ፤ በመሆኑም ከእያንዳንዱ ነገድ አንድ አንድ ሰው ይኸውም ከመካከላችሁ 12 ሰዎችን መረጥኩ።
እነሱም ተነስተው ወደ ተራራማው አካባቢ ሄዱ፤ እስከ ኤሽኮል ሸለቆ ድረስ በመዝለቅም ምድሪቱን ሰለሉ።
ምድሪቱ ከምታፈራው ፍሬም የተወሰነ ይዘው ወደ እኛ መጡ፤ እንዲሁም ‘አምላካችን ይሖዋ የሚሰጠን ምድር መልካም ናት’ ብለው ነገሩን።
እናንተ ግን ወደዚያ ለመውጣት ፈቃደኞች አልሆናችሁም፤ በአምላካችሁ በይሖዋ ትእዛዝም ላይ ዓመፃችሁ።
በየድንኳኖቻችሁ ውስጥ ሆናችሁ እንዲህ በማለት አጉተመተማችሁ፦ ‘ይሖዋ ስለጠላን አሞራውያን እንዲያጠፉን ለእነሱ አሳልፎ ሊሰጠን ከግብፅ ምድር አወጣን።
ታዲያ የምንሄደው ወዴት ነው? ወንድሞቻችን “ሰዎቹ ከእኛ ይልቅ ብርቱና ረጃጅሞች ናቸው፤ ከተሞቻቸውም ቢሆኑ ታላላቅና እስከ ሰማይ በሚደርስ ቅጥር የታጠሩ ናቸው፤ እንዲያውም በዚያ የኤናቅን ልጆች አይተናል” በማለት ልባችን እንዲቀልጥ አድርገዋል።’
“በመሆኑም እኔ እንዲህ አልኳችሁ፦ ‘በእነሱ የተነሳ በፍርሃት አትራዱ ወይም አትሸበሩ።
አምላካችሁ ይሖዋ በፊታችሁ ይሄዳል፤ የገዛ ዓይናችሁ እያየ በግብፅ እንዳደረገው ሁሉ አሁንም ይዋጋላችኋል።
በምድረ በዳም ተጉዛችሁ እዚህ እስክትደርሱ ድረስ አንድ አባት ልጁን እንደሚሸከም አምላካችሁ ይሖዋም በሄዳችሁበት ሁሉ እንዴት እንደተሸከማችሁ አይታችኋል።’
እናንተ ግን ይህ ሁሉ ተደርጎላችሁም በአምላካችሁ በይሖዋ ላይ እምነት አላሳደራችሁም፤
እሱ የምትሰፍሩበትን ቦታ ለመፈለግ ከፊት ከፊታችሁ ይሄድ ነበር። በየትኛው መንገድ መሄድ እንዳለባችሁ ለማሳየትም ሌሊት ሌሊት በእሳት፣ ቀን ቀን ደግሞ በደመና ይመራችሁ ነበር።
“በዚህ ጊዜ ይሖዋ ያላችሁትን ሰማ፤ ተቆጥቶም እንዲህ ሲል ማለ፦
‘ለአባቶቻችሁ ለመስጠት የማልኩላቸውን መልካሚቱን ምድር ከዚህ ክፉ ትውልድ መካከል አንድም ሰው አያያትም፤
ከየፎኒ ልጅ ከካሌብ በስተቀር ማንም አያያትም። እሱ ያያታል፤ ይሖዋን በሙሉ ልቡ ስለተከተለም የረገጣትን ምድር ለእሱና ለልጆቹ እሰጣታለሁ።
(ይሖዋ በእናንተ የተነሳ በእኔም ላይ እንኳ ተቆጥቶ እንዲህ አለኝ፦ “አንተም ብትሆን ወደዚያ አትገባም።
ወደ ምድሪቱ የሚገባው በፊትህ የሚቆመው የነዌ ልጅ ኢያሱ ነው። እስራኤላውያን ምድሪቱን እንዲወርሱ የሚያደርገው እሱ ስለሆነ አበርታው።”)
በተጨማሪም ለምርኮ ይዳረጋሉ ያላችኋቸው ልጆቻችሁ እንዲሁም ዛሬ ክፉና ደጉን የማያውቁት ወንዶች ልጆቻችሁ ወደዚያ ይገባሉ፤ እኔም ምድሪቱን እንዲወርሷት ለእነሱ እሰጣታለሁ።
እናንተ ግን አቅጣጫ በመቀየር ወደ ቀይ ባሕር በሚወስደው መንገድ አድርጋችሁ ወደ ምድረ በዳው ሂዱ።’
“እናንተም በዚህ ጊዜ እንዲህ አላችሁኝ፦ ‘በይሖዋ ላይ ኃጢአት ሠርተናል። በቃ፣ አምላካችን ይሖዋ ባዘዘን መሠረት ወጥተን እንዋጋለን!’ በመሆኑም እያንዳንዳችሁ የጦር መሣሪያዎቻችሁን ታጠቃችሁ፤ ወደ ተራራው መውጣት ቀላል መስሎ ታይቷችሁ ነበር።
ይሁንና ይሖዋ እንዲህ አለኝ፦ ‘እንዲህ በላቸው፦ “እኔ አብሬያችሁ ስለማልሆን ወጥታችሁ ውጊያ እንዳትገጥሙ። እንዲህ ብታደርጉ ግን ጠላቶቻችሁ ድል ያደርጓችኋል።”’
እኔም ነገርኳችሁ፤ እናንተ ግን አልሰማችሁም። ከዚህ ይልቅ በይሖዋ ትእዛዝ ላይ በማመፅ በእብሪት ወደ ተራራው ለመውጣት ሞከራችሁ።
ከዚያም በተራራው ላይ ይኖሩ የነበሩት አሞራውያን እናንተን ለመግጠም ወጡ፤ እነሱም ልክ እንደ ንብ እየተከታተሉ አሳደዷችሁ፤ ከሴይር አንስቶ እስከ ሆርማ ድረስም በታተኗችሁ።
ስለሆነም ተመልሳችሁ በይሖዋ ፊት ማልቀስ ጀመራችሁ፤ ሆኖም ይሖዋ ጩኸታችሁን አልሰማም፤ ጆሮውንም አልሰጣችሁም።
እነዚያን ሁሉ ቀናት በቃዴስ የተቀመጣችሁትም ለዚህ ነው።
“አምላክህ ይሖዋ ርስት አድርገህ ወደምትወርሳት ምድር ሲያመጣህ ብዙ ሕዝብ ያላቸውን ብሔራት ይኸውም ከአንተ ይልቅ ብዙ ሕዝብ ያላቸውንና ኃያላን የሆኑትን ሰባት ብሔራት ማለትም ሂታውያንን፣ ገርጌሻውያንን፣ አሞራውያንን፣ ከነአናውያንን፣ ፈሪዛውያንን፣ ሂዋውያንን እና ኢያቡሳውያንን ከፊትህ ያስወግድልሃል።
አምላክህ ይሖዋ እነሱን አሳልፎ ይሰጥሃል፤ ድልም ታደርጋቸዋለህ። አንተም ሙሉ በሙሉ ደምስሳቸው። ከእነሱ ጋር ምንም ዓይነት ቃል ኪዳን አትጋባ፤ አትራራላቸውም።
ከእነሱ ጋር በጋብቻ አትዛመድ። ሴቶች ልጆችህን ለወንዶች ልጆቻቸው አትዳር ወይም ሴቶች ልጆቻቸውን ለወንዶች ልጆችህ አትውሰድ።
ምክንያቱም ልጆችህ ሌሎች አማልክትን ያገለግሉ ዘንድ እኔን ከመከተል ዞር እንዲሉ ያደርጓቸዋል፤ ከዚያም የይሖዋ ቁጣ በእናንተ ላይ ይነድዳል፤ አንተንም ወዲያው ያጠፋሃል።
“ከዚህ ይልቅ እንዲህ አድርጉባቸው፦ መሠዊያዎቻቸውን አፈራርሱ፤ የማምለኪያ ዓምዶቻቸውን ሰባብሩ፤ የማምለኪያ ግንዶቻቸውን ቆራርጡ፤ የተቀረጹ ምስሎቻቸውንም በእሳት አቃጥሉ።
ምክንያቱም አንተ ለአምላክህ ለይሖዋ ቅዱስ ሕዝብ ነህ፤ አምላክህ ይሖዋ በምድር ላይ ካሉ ሕዝቦች ሁሉ መካከል አንተን የራሱ ሕዝብ፣ ልዩ ንብረቱ እንድትሆን መርጦሃል።
“ይሖዋ እናንተን የወደዳችሁና የመረጣችሁ ከሌሎች ሕዝቦች ሁሉ ይልቅ ቁጥራችሁ ስለበዛ አይደለም፤ ቁጥራችሁማ ከሌሎች ሕዝቦች ሁሉ አነስተኛ ነበር።
ከዚህ ይልቅ ይሖዋ እናንተን ከባርነት ቤት ይኸውም ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን እጅ ይታደጋችሁ ዘንድ ይሖዋ በብርቱ እጅ ያወጣችሁ ስለወደዳችሁና ለአባቶቻችሁ የማለላቸውን መሐላ ስለጠበቀ ነው።
አንተም አምላክህ ይሖዋ እውነተኛ አምላክ፣ ታማኝ አምላክ እንዲሁም ለሚወዱትና ትእዛዛቱን ለሚጠብቁ ሁሉ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ቃል ኪዳኑን የሚጠብቅና ታማኝ ፍቅር የሚያሳይ መሆኑን በሚገባ ታውቃለህ።
የሚጠሉትን ግን በማጥፋት በግልጽ ይበቀላቸዋል። በሚጠሉት ላይ እርምጃ ለመውሰድ አይዘገይም፤ በግልጽ ይበቀላቸዋል።
ስለዚህ እኔ ዛሬ የማዝህን ትእዛዛት፣ ሥርዓቶችና ድንጋጌዎች በማክበር በጥንቃቄ ጠብቃቸው።
“እነዚህን ድንጋጌዎች ብትሰሙና ብትጠብቋቸው እንዲሁም ብትፈጽሟቸው አምላካችሁ ይሖዋ ለአባቶቻችሁ በመሐላ የገባውን ቃል ኪዳንና ታማኝ ፍቅር ይጠብቃል።
ይወድሃል፣ ይባርክሃል እንዲሁም ያበዛሃል። አዎ፣ ለአንተ ሊሰጥህ ለአባቶችህ በማለላቸው ምድር ላይ የሆድህን ፍሬ፣ የመሬትህን ምርት፣ እህልህን፣ አዲሱን የወይን ጠጅህን፣ ዘይትህን፣ የከብቶችህን ጥጆችና የመንጋህን ግልገሎች ይባርክልሃል።
አንተም ከሕዝቦች ሁሉ ይበልጥ የተባረክ ትሆናለህ፤ በመካከልህ ልጅ የሌለው ወንድ ወይም ሴት አይገኝም፤ እንስሶችህም ግልገል የሌላቸው አይሆኑም።
ይሖዋ በሽታን ሁሉ ያስወግድልሃል፤ በግብፅ ሳለህ ታውቃቸው ከነበሩት አሰቃቂ በሽታዎች አንዱንም በአንተ ላይ አያመጣም። ከዚህ ይልቅ በሚጠሉህ ሁሉ ላይ ያመጣባቸዋል።
አምላክህ ይሖዋ አሳልፎ የሚሰጥህን ሕዝቦች ሁሉ ታጠፋለህ። አትዘንላቸው፤ አማልክታቸውንም አታገልግል፤ ምክንያቱም እንዲህ ማድረግህ ወጥመድ ይሆንብሃል።
“ምናልባት በልብህ ‘እነዚህ ብሔራት እኮ ከእኛ ይልቅ ብዙ ናቸው። ታዲያ እንዴት ላባርራቸው እችላለሁ?’ ትል ይሆናል፤
ሆኖም አትፍራቸው። አምላክህ ይሖዋ በፈርዖንና በግብፅ ሁሉ ላይ ያደረገውን አስታውስ፤
ዓይኖችህ ያዩአቸውን ታላላቅ የፍርድ እርምጃዎች እንዲሁም አምላክህ ይሖዋ አንተን ለማውጣት የተጠቀመባቸውን ድንቅ ምልክቶች፣ ተአምራት፣ ብርቱ እጅና የተዘረጋ ክንድ አስብ። አምላክህ ይሖዋ በምትፈራቸው ሕዝቦች ሁሉ ላይ የሚያደርገው ይህንኑ ነው።
አምላክህ ይሖዋ በሕይወት የተረፉትና ከፊትህ የተሸሸጉት እስኪጠፉ ድረስ ጭንቀት ይለቅባቸዋል።
ታላቅና የሚያስፈራ አምላክ የሆነው አምላክህ ይሖዋ ከአንተ ጋር ስለሆነ በእነሱ የተነሳ አትሸበር።
“አምላክህ ይሖዋ እነዚህን ብሔራት በጥቂት በጥቂቱ ከፊትህ ያባርራቸዋል። የዱር አራዊት እንዳይበዙብህ በአንድ ጊዜ ጠራርገህ እንድታጠፋቸው አይፈቀድልህም።
አምላክህ ይሖዋ እነሱን በእጅህ አሳልፎ ይሰጥሃል፤ እስኪጠፉም ድረስ ሙሉ በሙሉ ድል ታደርጋቸዋለህ።