text
stringlengths
4
267
ቢንያማውያን ግን በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ኢያቡሳውያን ከዚያ አላስወጧቸውም ነበር፤ በመሆኑም ኢያቡሳውያኑ ከቢንያማውያን ጋር እስከ ዛሬ ድረስ በኢየሩሳሌም አብረው ይኖራሉ።
በዚህ ጊዜ የዮሴፍ ቤት ቤቴልን ለመውጋት ወጣ፤ ይሖዋም ከእነሱ ጋር ነበር።
የዮሴፍ ቤት ቤቴልን እየሰለለ ነበር (ቤቴል ቀደም ሲል ሎዛ ተብላ ትጠራ ነበር)፤
ሰላዮቹም አንድ ሰው ከከተማዋ ሲወጣ አዩ። በመሆኑም “እባክህ ወደ ከተማዋ የሚያስገባውን መንገድ አሳየን፤ እኛም ደግነት እናደርግልሃለን” አሉት።
በመሆኑም ሰውየው ወደ ከተማዋ የሚያስገባውን መንገድ አሳያቸው፤ እነሱም የከተማዋን ነዋሪዎች በሰይፍ መቱ፤ ይሁንና ሰውየውንና ቤተሰቡን በሙሉ ነፃ ለቀቋቸው።
ሰውየውም ወደ ሂታውያን ምድር ሄዶ ከተማ ገነባ፤ ከተማዋንም ሎዛ ብሎ ጠራት፤ እስከ ዛሬም ድረስ ስሟ ይኸው ነው።
ምናሴ ቤትሼንንና በሥሯ ያሉትን ከተሞች፣ ታአናክንና በሥሯ ያሉትን ከተሞች፣ የዶርን ነዋሪዎችና በሥሯ ያሉትን ከተሞች፣ የይብለአምን ነዋሪዎችና በሥሯ ያሉትን ከተሞች እንዲሁም የመጊዶን ነዋሪዎችና በሥሯ ያሉትን ከተሞች አልወረሰም ነበር። ከነአናውያን ይህን ምድር ላለመልቀቅ ቆርጠው ነበር።
እስራኤላውያንም እያየሉ በሄዱ ጊዜ ከነአናውያንን የግዳጅ ሥራ እንዲሠሩ አስገደዷቸው እንጂ ሙሉ በሙሉ አላባረሯቸውም።
ኤፍሬምም ቢሆን በጌዜር ይኖሩ የነበሩትን ከነአናውያን አላባረራቸውም። ከነአናውያን በጌዜር አብረዋቸው ይኖሩ ነበር።
ዛብሎንም የቂትሮንን ነዋሪዎችና የናሃሎልን ነዋሪዎች አላባረራቸውም። ከነአናውያን አብረዋቸው ይኖሩ የነበረ ሲሆን የግዳጅ ሥራም እንዲሠሩ ተገደው ነበር።
አሴር የአኮን ነዋሪዎች እንዲሁም የሲዶናን፣ የአህላብን፣ የአክዚብን፣ የሄልባን፣ የአፊቅን እና የሬሆብን ነዋሪዎች አላባረራቸውም።
በመሆኑም አሴራውያን በምድሩ ይኖሩ ከነበሩት ከነአናውያን ጋር አብረው መኖራቸውን ቀጠሉ፤ ምክንያቱም አላባረሯቸውም ነበር።
ንፍታሌም የቤትሼሜሽን ነዋሪዎችና የቤትአናትን ነዋሪዎች አላባረራቸውም፤ ከዚህ ይልቅ በምድሩ ይኖሩ ከነበሩት ከነአናውያን ጋር አብረው ኖሩ። የቤትሼሜሽ ነዋሪዎችና የቤትአናት ነዋሪዎች የግዳጅ ሥራ ይሠሩላቸው ነበር።
ዳናውያን ወደ ሜዳው እንዲወርዱ አሞራውያን ስላልፈቀዱላቸው በተራራማው አካባቢ ተወስነው ለመኖር ተገደዱ።
አሞራውያን የሃሬስ ተራራን፣ አይሎንን እና ሻአልቢምን አንለቅም በማለት በዚያ መኖራቸውን ቀጠሉ። ይሁንና የዮሴፍ ቤት ኃይሉ እየጨመረ በመጣ ጊዜ የጉልበት ሥራ ለመሥራት ተገደዱ።
የአሞራውያን ክልል ከአቅራቢም አቀበትና ከሴላ አንስቶ ወደ ላይ ያለው ነበር።
ከዚያም የሩባአል የተባለው ጌድዮንና ከእሱ ጋር የነበሩት ሰዎች በሙሉ በማለዳ ተነስተው በሃሮድ ምንጭ አጠገብ ሰፈሩ፤ የምድያማውያን ሰፈር ደግሞ ከእሱ በስተ ሰሜን በሞሬ ኮረብታ በሸለቋማው ሜዳ ላይ ይገኝ ነበር።
ይሖዋም ጌድዮንን እንዲህ አለው፦ “ምድያማውያንን በእጃቸው አሳልፌ እንዳልሰጥ አብረውህ ያሉት ሰዎች በጣም ብዙ ናቸው። ይህን ባደርግ እስራኤላውያን ‘የገዛ እጄ አዳነኝ’ ብለው ይታበዩብኛል።
በመሆኑም እባክህ ሕዝቡ በተሰበሰበበት ‘ከመካከላችሁ የፈራና የተሸበረ ካለ ወደ ቤት ይመለስ’ ብለህ ተናገር።” ስለዚህ ጌድዮን ፈተናቸው። በዚህ ጊዜ ከሕዝቡ መካከል 22,000 ሰዎች ወደ ቤታቸው ተመለሱና 10,000 ብቻ ቀሩ።
ይሖዋም እንደገና ጌድዮንን እንዲህ አለው፦ “አሁንም ሰዎቹ በጣም ብዙ ናቸው። በዚያ እነሱን እንድፈትንልህ ወደ ውኃው ይዘሃቸው ውረድ። እኔም ‘ይህ ከአንተ ጋር ይሄዳል’ የምልህ ከአንተ ጋር ይሄዳል፤ ‘ይህ ከአንተ ጋር አይሄድም’ የምልህ ግን ከአንተ ጋር አይሄድም።”
እሱም ሰዎቹን ወደ ውኃው ይዟቸው ወረደ። ከዚያም ይሖዋ ጌድዮንን “ልክ እንደ ውሻ ውኃውን በምላሱ እየጨለፈ የሚጠጣውን ሁሉ በጉልበታቸው ተንበርክከው ከሚጠጡት ለይ” አለው።
ውኃውን በእጃቸው እየጨለፉ የሚጠጡት ሰዎች ቁጥር 300 ነበር። የቀሩት ሰዎች ሁሉ ግን ውኃ ለመጠጣት በጉልበታቸው ተንበረከኩ።
ይሖዋም ጌድዮንን እንዲህ አለው፦ “ውኃውን በእጃቸው እየጨለፉ በጠጡት 300 ሰዎች አድናችኋለሁ፤ ምድያማውያንንም በእጃችሁ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ። የቀሩት ሰዎች ሁሉ ግን ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ አሰናብታቸው።”
በመሆኑም ከሕዝቡ ላይ ስንቃቸውንና ቀንደ መለከታቸውን ከተቀበሉ በኋላ ጌድዮን 300ዎቹን ብቻ አስቀርቶ ሌሎቹን እስራኤላውያን በሙሉ ወደ ቤታቸው አሰናበታቸው። የምድያማውያኑ ሰፈር የሚገኘው ከእሱ በታች በሸለቋማው ሜዳ ላይ ነበር።
በዚያ ምሽት ይሖዋ ጌድዮንን እንዲህ አለው፦ “ተነስ፤ በእጅህ አሳልፌ ስለሰጠሁህ በሰፈሩ ላይ ጥቃት ሰንዝር።
በሰፈሩ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ከፈራህ ግን ከአገልጋይህ ከፑራ ጋር ወደ ሰፈሩ ውረድ።
የሚናገሩትንም ነገር አዳምጥ፤ ከዚያም በሰፈሩ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ድፍረት ታገኛለህ።” ስለዚህ እሱና አገልጋዩ ፑራ ወርደው ሠራዊቱ ወደሰፈረበት ቦታ ተጠጉ።
ምድያማውያንና አማሌቃውያን እንዲሁም የምሥራቅ ሰዎች በሙሉ ሸለቋማውን ሜዳ ልክ እንደ አንበጣ መንጋ ወረውት ነበር፤ ግመሎቻቸውም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ለቁጥር የሚያታክቱ ነበሩ።
ጌድዮንም እዚያ ደረሰ፤ በዚህ ጊዜ አንድ ሰው ለጓደኛው እንዲህ በማለት አንድ ሕልም እየነገረው ነበር፦ “ያለምኩት ሕልም ይህ ነው። አንድ የገብስ ዳቦ እየተንከባለለ ወደ ምድያም ሰፈር መጣ። ከዚያም ወደ አንድ ድንኳን በመምጣት በኃይል መትቶ ጣለው። ድንኳኑንም ገለበጠው፤ ድንኳኑም መሬት ላይ ተነጠፈ።”
ጓደኛውም እንዲህ አለው፦ “ይሄማ ከዮአስ ልጅ ከእስራኤላዊው ከጌድዮን ሰይፍ በስተቀር ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም። አምላክ ምድያማውያንንና ሰፈሩን በሙሉ በእጁ አሳልፎ ሰጥቶታል።”
ጌድዮንም ሕልሙንና ፍቺውን ሲሰማ ለአምላክ ሰገደ። ከዚያም ወደ እስራኤላውያን ሰፈር ተመልሶ “ተነሱ፤ ይሖዋ የምድያማውያንን ሰፈር በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቷችኋል” አላቸው።
በመቀጠልም 300ዎቹን ሰዎች በሦስት ቡድን ከፈላቸው፤ ለሁሉም ቀንደ መለከትና በውስጣቸው ችቦ ያለባቸው ትላልቅ ባዶ ማሰሮዎች ሰጣቸው።
ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “ልብ ብላችሁ ተመልከቱኝ፤ እኔ የማደርገውንም አድርጉ። ወደ ሰፈሩ ዳርቻ በምጠጋበት ጊዜ ልክ እኔ እንደማደርገው አድርጉ።
እኔና ከእኔ ጋር ያሉት ሁሉ ቀንደ መለከቶቻችንን ስንነፋ እናንተም በሰፈሩ ዙሪያ ሁሉ ቀንደ መለከቶቻችሁን ነፍታችሁ ‘ለይሖዋና ለጌድዮን!’ ብላችሁ ጩኹ።”
ከዚያም ጌድዮንና ከእሱ ጋር የነበሩት 100 ሰዎች በመካከለኛው ክፍለ ሌሊት መጀመሪያ ላይ ዘብ ጠባቂዎቹ ገና እንደተቀያየሩ ወደ ሰፈሩ ዳርቻ ተጠጉ። እነሱም ቀንደ መለከቶቻቸውን ነፉ፤ የያዟቸውንም ትላልቅ የውኃ ማሰሮዎች ሰባበሩ።
በዚህ ጊዜ ሦስቱም ቡድኖች ቀንደ መለከቶቻቸውን ነፉ፤ ትላልቆቹንም ማሰሮዎች ሰባበሩ። ችቦዎቹን በግራ እጃቸው ይዘው በቀኝ እጃቸው የያዟቸውን ቀንደ መለከቶች እየነፉ “የይሖዋና የጌድዮን ሰይፍ!” በማለት ጮኹ።
እያንዳንዱም ሰው በሰፈሩ ዙሪያ ቦታ ቦታውን ይዞ ቆሞ ነበር፤ ሠራዊቱም ሁሉ ሮጠ፤ እየጮኸም ሸሸ።
ሦስት መቶዎቹ ሰዎችም ቀንደ መለከቶቹን መንፋታቸውን ቀጠሉ፤ ይሖዋም በሰፈሩ ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ሰው አንዱ በሌላው ላይ ሰይፉን እንዲመዝበት አደረገ፤ ሠራዊቱም በጸሬራህ አቅጣጫ እስከ ቤትሺጣ እንዲሁም ከጣባት አጠገብ እስከምትገኘው እስከ አቤልምሆላ ዳርቻ ድረስ ሸሸ።
እስራኤላውያንም ከንፍታሌም፣ ከአሴርና ከመላው ምናሴ ተጠርተው አንድ ላይ በመሰባሰብ ምድያማውያንን አሳደዷቸው።
ጌድዮንም በኤፍሬም ተራራማ አካባቢዎች ለሚኖሩ ሁሉ “በምድያማውያን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ውረዱ፤ እስከ ቤትባራ ድረስ ያሉትን ውኃዎችና ዮርዳኖስን ያዙ” ብለው እንዲነግሯቸው መልእክተኞችን ላከ። በመሆኑም የኤፍሬም ሰዎች በሙሉ ተጠሩ፤ እነሱም እስከ ቤትባራ ድረስ ያሉትን ውኃዎችና ዮርዳኖስን ያዙ።
በተጨማሪም ሁለቱን የምድያም መኳንንት ማለትም ኦሬብን እና ዜብን ያዙ፤ ኦሬብን በኦሬብ ዓለት ላይ ገደሉት፤ ዜብን ደግሞ በዜብ የወይን መጭመቂያ ላይ ገደሉት። ምድያማውያንንም ማሳደዳቸውን ተያያዙት፤ የኦሬብን እና የዜብን ጭንቅላት በዮርዳኖስ አካባቢ ወደነበረው ወደ ጌድዮን አመጡ።
እስራኤላውያን እንደገና በይሖዋ ፊት መጥፎ ነገር አደረጉ፤ ይሖዋም ለ40 ዓመት በፍልስጤማውያን እጅ አሳልፎ ሰጣቸው።
በዚህ ጊዜ ከዳናውያን ቤተሰብ የሆነ ስሙ ማኑሄ የሚባል አንድ የጾራ ሰው ነበር። ሚስቱ መሃን ስለነበረች ልጅ አልነበራትም።
ከጊዜ በኋላ የይሖዋ መልአክ ለሴቲቱ ተገለጠላትና እንዲህ አላት፦ “እነሆ አንቺ መሃን ነሽ፤ ልጅም የለሽም። ነገር ግን ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ።
እንግዲህ ተጠንቀቂ፤ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጪ፤ እንዲሁም ምንም ዓይነት ርኩስ ነገር አትብዪ።
እነሆ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ይህ ልጅ ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ የአምላክ ናዝራዊ ስለሚሆን ራሱን ምላጭ አይንካው፤ እሱም እስራኤልን ከፍልስጤማውያን እጅ በማዳን ረገድ ግንባር ቀደም ይሆናል።”
ከዚያም ሴቲቱ ሄዳ ባሏን እንዲህ አለችው፦ “የእውነተኛው አምላክ ሰው ወደ እኔ መጥቶ ነበር፤ መልኩም የእውነተኛውን አምላክ መልአክ ይመስላል፤ በጣም የሚያስፈራ ነበር። ከየት እንደመጣ አልጠየቅኩትም፤ እሱም ቢሆን ስሙን አልነገረኝም።
ሆኖም እንዲህ አለኝ፦ ‘እነሆ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ። እንግዲህ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጪ፤ እንዲሁም ምንም ዓይነት ርኩስ ነገር አትብዪ፤ ምክንያቱም ልጁ ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ እስከሚሞትበት ዕለት ድረስ የአምላክ ናዝራዊ ይሆናል።’”
ማኑሄም “ይቅርታ አድርግልኝ ይሖዋ። እባክህ ልከኸው የነበረው ያ የእውነተኛው አምላክ ሰው እንደገና ወደ እኛ ይምጣና የሚወለደውን ልጅ በተመለከተ ምን ማድረግ እንዳለብን መመሪያ ይስጠን” በማለት ይሖዋን ተማጸነ።
በመሆኑም እውነተኛው አምላክ የማኑሄን ቃል ሰማ፤ የእውነተኛው አምላክ መልአክም ሴቲቱ ሜዳ ላይ ተቀምጣ ሳለ ዳግመኛ ወደ እሷ መጣ፤ ባሏ ማኑሄ ግን አብሯት አልነበረም።
ሴቲቱም በፍጥነት እየሮጠች ሄዳ ባሏን “ባለፈው ጊዜ ወደ እኔ መጥቶ የነበረው ሰው ተገለጠልኝ” አለችው።
ከዚያም ማኑሄ ተነስቶ ከሚስቱ ጋር ሄደ። ሰውየውንም ሲያገኘው “ሚስቴን ያነጋገርካት አንተ ነህ?” አለው፤ እሱም “አዎ፣ እኔ ነኝ” አለ።
ማኑሄም “እንግዲህ እንደ ቃልህ ይሁንልን! ይሁንና ልጁን ማሳደግ የሚኖርብን እንዴት ነው? የእሱስ ሥራ ምን ይሆናል?” አለው።
የይሖዋም መልአክ ማኑሄን እንዲህ አለው፦ “ሚስትህ ከነገርኳት ነገር ሁሉ ራሷን ትጠብቅ።
ከወይን ተክል የሚገኝ ማንኛውንም ነገር አትብላ፤ የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጣ፤ እንዲሁም ምንም ዓይነት ርኩስ ነገር አትብላ። ያዘዝኳትን ሁሉ ትጠብቅ።”
ማኑሄም የይሖዋን መልአክ “እባክህ አንድ የፍየል ጠቦት አዘጋጅተን እስክናቀርብልህ ድረስ ቆይ” አለው።
ሆኖም የይሖዋ መልአክ ማኑሄን “ብቆይም እንኳ የምታቀርበውን ምግብ አልበላም፤ ይሁንና ለይሖዋ የሚቃጠል መባ ማቅረብ የምትፈልግ ከሆነ እሱን አቅርበው” አለው። ማኑሄ ይህ ሰው የይሖዋ መልአክ መሆኑን አላወቀም ነበር።
ከዚያም ማኑሄ የይሖዋን መልአክ “የተናገርከው ቃል ሲፈጸም እንድናከብርህ ስምህ ማን ነው?” በማለት ጠየቀው።
ሆኖም የይሖዋ መልአክ “ስሜ የሚያስደንቅ ሆኖ ሳለ ለምን ስሜን ትጠይቀኛለህ?” አለው።
ከዚያም ማኑሄ የፍየል ጠቦቱንና የእህል መባውን ወስዶ በዓለቱ ላይ ለይሖዋ አቀረበው። እሱም ማኑሄና ሚስቱ እየተመለከቱ አስደናቂ ነገር አደረገ።
የእሳቱ ነበልባል ከመሠዊያው ወደ ሰማይ ሲወጣ የይሖዋ መልአክ ማኑሄና ሚስቱ እያዩት ከመሠዊያው በወጣው ነበልባል ውስጥ ሆኖ አረገ። እነሱም ወዲያውኑ በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፉ።
የይሖዋም መልአክ ለማኑሄና ለሚስቱ ዳግመኛ አልተገለጠላቸውም። ማኑሄ ሰውየው የይሖዋ መልአክ እንደነበር የተገነዘበው ያን ጊዜ ነበር።
ከዚያም ማኑሄ ሚስቱን “ያየነው አምላክን ስለሆነ መሞታችን አይቀርም” አላት።
ሚስቱ ግን “ይሖዋ ሊገድለን ቢፈልግማ ኖሮ የሚቃጠል መባና የእህል መባ ከእጃችን ባልተቀበለ ነበር፤ ደግሞም ይህን ሁሉ ነገር ባላሳየንና እንዲህ ያለውንም ነገር ባልነገረን ነበር” አለችው።
በኋላም ሴቲቱ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሳምሶን አለችው፤ ልጁም እያደገ ሄደ፤ ይሖዋም ባረከው።
ከጊዜ በኋላም በጾራ እና በኤሽታዖል መካከል በምትገኘው በማሃነህዳን ሳለ የይሖዋ መንፈስ ይገፋፋው ጀመር።
የእስራኤል ሰዎች በምጽጳ ተሰብስበው “ከእኛ መካከል ማንም ሰው ሴት ልጁን ከቢንያም ወገን ለሆነ ሰው መዳር የለበትም” በማለት ተማምለው ነበር።
በመሆኑም እስራኤላውያን ወደ ቤቴል መጥተው በዚያ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አምርረው እያለቀሱ በእውነተኛው አምላክ ፊት እስከ ምሽት ድረስ ተቀመጡ።
እነሱም “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ በእስራኤል ውስጥ እንዲህ ያለ ነገር እንዲከሰት ለምን ፈቀድክ? ዛሬ ከእስራኤል መካከል አንድ ነገድ እንዴት ይጥፋ?” ይሉ ነበር።
በማግስቱም ሕዝቡ በማለዳ ተነስቶ የሚቃጠሉ መባዎችንና የኅብረት መባዎችን ለማቅረብ በዚያ መሠዊያ ሠራ።
የእስራኤል ሰዎችም በምጽጳ በይሖዋ ፊት ያልተገኘ ሰው ሁሉ ያለምንም ጥርጥር መገደል አለበት በማለት በጥብቅ ተማምለው ስለነበር “ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ መካከል በይሖዋ ፊት ለመሰብሰብ ያልወጣው ማን ነው?” በማለት ጠየቁ።
የእስራኤል ሰዎችም በወንድማቸው በቢንያም ላይ በደረሰው ነገር አዘኑ። እንዲህም አሉ፦ “እነሆ ዛሬ ከእስራኤል መካከል አንድ ነገድ ተቆርጧል።
እንግዲህ እኛ ሴት ልጆቻችንን ለእነሱ ላለመዳር በይሖዋ ምለናል፤ ታዲያ የተረፉት ወንዶች ሚስት ማግኘት እንዲችሉ ምን ብናደርግ ይሻላል?”
እነሱም “ከእስራኤል ነገዶች መካከል በምጽጳ በይሖዋ ፊት ለመቅረብ ያልወጣው የትኛው ነው?” በማለት ጠየቁ። ከኢያቢስጊልያድ ጉባኤው ወደነበረበት ሰፈር የመጣ ማንም ሰው አልነበረም።
ሕዝቡ በተቆጠረበት ጊዜ ከኢያቢስጊልያድ ነዋሪዎች መካከል አንድም ሰው እንዳልነበር ተገነዘቡ።
በመሆኑም ማኅበረሰቡ እጅግ ኃያል ከሆኑት ተዋጊዎች መካከል 12,000 ሰዎችን ወደዚያ ላከ። እንዲህም ሲሉ አዘዟቸው፦ “ሂዱ፤ የኢያቢስጊልያድን ነዋሪዎች በሰይፍ ምቱ፤ ሴቶችንና ልጆችንም እንኳ አታስቀሩ።
እንግዲህ እንዲህ አድርጉ፦ እያንዳንዱን ወንድ እንዲሁም ከወንድ ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጽመው የሚያውቁ ሴቶችን ሁሉ ፈጽማችሁ አጥፉ።”
እነሱም ከኢያቢስጊልያድ ነዋሪዎች መካከል ከወንድ ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጽመው የማያውቁ 400 ደናግል ሴቶችን አገኙ። እነሱንም በከነአን ምድር በሴሎ ወደሚገኘው ሰፈር አመጧቸው።
ከዚያም መላው ማኅበረሰብ በሪሞን በሚገኘው ዓለት ወዳሉት ቢንያማውያን መልእክት በመላክ የሰላም ጥሪ አቀረበላቸው።
በመሆኑም በዚህ ጊዜ ቢንያማውያን ወደ ምድራቸው ተመለሱ። ከኢያቢስጊልያድ ሴቶች መካከል በሕይወት እንዲተርፉ የተዉአቸውንም ሴቶች ሰጧቸው፤ ሆኖም በቂ ሴቶች አላገኙላቸውም።
ሕዝቡም ይሖዋ በእስራኤል ነገዶች መካከል ክፍፍል እንዲኖር በማድረጉ የተነሳ በቢንያማውያን ላይ በደረሰው ነገር አዘነ።
የማኅበረሰቡም ሽማግሌዎች “ቢንያማውያን ሴቶች በሙሉ ስላለቁ ለተረፉት ወንዶች ሚስት ለማግኘት ምን ብናደርግ ይሻላል?” አሉ።
እነሱም እንዲህ በማለት መለሱ፦ “ከእስራኤል መካከል አንድ ነገድ ሙሉ በሙሉ እንዳይጠፋ በሕይወት ለተረፉት ቢንያማውያን ርስት ሊኖራቸው ይገባል።
ሆኖም እኛ ሴቶች ልጆቻችንን ለእነሱ መዳር አይፈቀድልንም፤ ምክንያቱም የእስራኤል ሰዎች ‘ለቢንያም ልጁን የሚድር የተረገመ ነው’ ብለው ምለዋል።”
ከዚያም “ከቤቴል በስተ ሰሜንና ከቤቴል ወደ ሴኬም ከሚወስደው አውራ ጎዳና በስተ ምሥራቅ እንዲሁም ከለቦና በስተ ደቡብ በምትገኘው በሴሎ በየዓመቱ ለይሖዋ የሚከበር በዓል አለ” አሉ።
በመሆኑም የቢንያምን ሰዎች እንዲህ በማለት አዘዟቸው፦ “ሂዱና በወይን እርሻው ውስጥ አድፍጣችሁ ጠብቁ።
የሴሎ ወጣት ሴቶች ክብ ሠርተው ለመጨፈር ሲወጡ ስታዩ እያንዳንዳችሁ ከወይን እርሻው ውስጥ ወጥታችሁ ከሴሎ ወጣት ሴቶች መካከል ለራሳችሁ ሚስት ጠልፋችሁ ውሰዱ፤ ከዚያም ወደ ቢንያም ምድር ተመለሱ።
አባቶቻቸው ወይም ወንድሞቻቸው መጥተው በእኛ ላይ ስሞታ ቢያሰሙ እንዲህ እንላቸዋለን፦ ‘ባደረግነው ጦርነት ለእያንዳንዳቸው የሚሆኑ ሚስቶችን ማግኘት ስላልቻልን ለእነሱ ስትሉ ውለታ ዋሉልን፤ እናንተም ብትሆኑ ሴቶቹን ፈቅዳችሁ ስላልሰጣችኋቸው በጥፋተኝነት አትጠየቁም።’”
በመሆኑም የቢንያም ሰዎች እንደተባሉት አደረጉ፤ እያንዳንዳቸውም ከሚጨፍሩት ሴቶች መካከል ሚስቶችን ጠልፈው ወሰዱ። ከዚያም ወደየርስታቸው ተመልሰው በመሄድ ከተሞቻቸውን በድጋሚ ገንብተው በዚያ መኖር ጀመሩ።
በዚያን ጊዜ እስራኤላውያን እያንዳንዳቸው ወደየነገዳቸውና ወደየቤተሰባቸው በመሄድ ከዚያ አካባቢ ተበተኑ፤ እያንዳንዳቸውም ከዚያ ተነስተው ወደየርስታቸው ሄዱ።
በዚያ ዘመን በእስራኤል ንጉሥ አልነበረም። እያንዳንዱም ሰው ለራሱ ትክክል መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር።
ይሖዋ ከከነአን ጋር በተደረገው ጦርነት ያልተካፈሉትን እስራኤላውያን ሁሉ እንዲፈትኗቸው ሲል በምድሪቱ ላይ እንዲኖሩ የፈቀደላቸው ብሔራት እነዚህ ናቸው
(ይህን ያደረገው ከዚህ በፊት ተዋግተው የማያውቁት በኋላ ላይ የመጡት የእስራኤላውያን ትውልዶች የውጊያ ልምድ እንዲያገኙ ነው)፦
አምስቱ የፍልስጤም ገዢዎች፣ ከነአናውያን በሙሉ፣ ሲዶናውያን እንዲሁም ከበዓልሄርሞን ተራራ አንስቶ እስከ ሌቦሃማት ድረስ በሚዘልቀው የሊባኖስ ተራራ የሚኖሩት ሂዋውያን።
እነዚህ ብሔራት እስራኤላውያን ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት ለአባቶቻቸው የሰጣቸውን ትእዛዛት ይጠብቁ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ የእስራኤላውያን መፈተኛ ሆነው አገልግለዋል።
በመሆኑም እስራኤላውያን በከነአናውያን፣ በሂታውያን፣ በአሞራውያን፣ በፈሪዛውያን፣ በሂዋውያን እና በኢያቡሳውያን መካከል ይኖሩ ነበር።
እነሱም ሴቶች ልጆቻቸውን ያገቡ፣ የራሳቸውንም ሴቶች ልጆች ለእነሱ ወንዶች ልጆች ይድሩ የነበረ ሲሆን የእነሱን አማልክትም ማገልገል ጀመሩ።
ስለዚህ እስራኤላውያን በይሖዋ ፊት መጥፎ ነገር አደረጉ፤ አምላካቸውን ይሖዋንም ረሱ፤ ባአልንና የማምለኪያ ግንዶችን አገለገሉ።
በዚህ ጊዜ የይሖዋ ቁጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፤ ለሜሶጶጣሚያው ንጉሥ ለኩሻንሪሻታይምም አሳልፎ ሸጣቸው። እስራኤላውያን ኩሻንሪሻታይምን ለስምንት ዓመት አገለገሉት።
ይሖዋ እንዲረዳቸው ወደ እሱ በጮኹም ጊዜ ይሖዋ እስራኤላውያንን እንዲያድናቸው የካሌብ ታናሽ ወንድም የሆነውን የቀናዝን ልጅ ኦትኒኤልን አዳኝ አድርጎ አስነሳው።